የኬንያ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ከአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ምክትል ሊቀመንበር ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 24፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኬንያ የቀድሞ ፕሬዚዳንት እና የአፍሪካ ሕብረት የምርጫ ታዛቢ ቡድን መሪ ኡሁሩ ኬንያታ ከአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ምክትል ሊቀመንበር አምባሳደር ሰልማ ማሊካ ሀዳዲ ጋር ተወያይተዋል።
በውይይቱ በኢትዮጵያ ጠቅላላ ምርጫ እና በአጠቃላይ የአፍሪካ ሕብረት የምርጫ ታዛቢ ልዑካን ሊያበረክቱ ሚችሉት ወሳኝ ሚና ዙሪያ መምከራቸውን ኡሁሩ ኬንያታ በማሕበራዊ የትስስር ገጻቸው ገልጸዋል።
የአፍሪካ ሕብረት የታዛቢ ቡድን መዋቅር ያለው አስፈላጊነትን በተመለከተ መወያየታቸውን ገልጸው÷ ተዓማኒ፣ ግልጽ እና ዴሞክራሲያዊ የምርጫ ሂደቶችን ለመደገፍ የተሰጣቸውን ኃላፊነት ሊወጡ እንደሚገባ አጽንኦት መሰጠቱን አመልክተዋል።
በተያያዘ መረጃ የአፍሪካ ሕብረት የምርጫ ታዛቢዎች ከምርጫው ቀደም ብለው በመላው ሀገሪቱ በመሰማራት ከባለድርሻ አካላት ጋር ተገናኝተው መወያየታቸውን የሕብረቱ መረጃ ያመላክታል፡፡
ከ37 የአፍሪካ ሀገራ የተሰባሰቡት ታዛቢዎቹ ውስጥ 61 ከመቶ የሚሆኑት ሴቶች ሲሆኑ÷ የሲቪል ማህበራት አባላት፣ የምርጫ ባለሙያዎች፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች እና የሚዲያ ባለሙያዎች እንዲሁም የወጣቶች ተወካዮች እንደሚገኙ ተገልጿል፡፡