Fana: At a Speed of Life!

በጤናው ዘርፍ የተከናወኑ መሠረተ ልማቶች ለጤና ቱሪዝም ማዕከልነት…

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 27፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በጤናው ዘርፍ የተከናወኑ የመሠረተ ልማት ግንባታዎችና የጥራት ማሻሻያዎች ኢትዮጵያን የጤና ቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ ትልቅ አቅም እየሆኑ መጥተዋል አሉ የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ደረጄ ዱጉማ።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኅብረተሰቡ ዘንድ የሚታየው የአኗኗር ዘይቤ መቀየር፣ የአመጋገብ ሥርዓት መዛባት እና የእንቅስቃሴ ውስንነት ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች በእጅጉ እንዲጨምሩ ምክንያት መሆናቸውን ገልጸዋል።

በመሆኑም በሽታዎቹን በተለያዩ ደረጃዎች ቀድሞ መለየትና አክሞ የማዳን አቅምን በዚያው ልክ ከፍ ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ አዲሱ የአክሞ ማዳን ፖሊሲ በትኩረት ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።

በሁሉም ደረጃ በሚገኙ የጤና ተቋማት የተሟላ የሕክምና ግብዓት እንዲሁም የሠለጠነ የሰው ኃይል በቁጥርም ሆነ በስብጥር እንዲኖራቸው በማድረግ የኅብረተሰቡን ጤና ለመጠበቅ የሚያስችሉ በርካታ ተግባራት መከናወናቸውንም አስታውቀዋል።

ትላልቅ ሆስፒታሎች ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ እንዲሆኑ የማድረግ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን ጠቅሰው÷ ሆስፒታሎቹ ከዚህ ቀደም በሀገር ውስጥ የማይሰጡ የላቁ የሕክምና አገልግሎቶችን በስፋት መስጠት መጀመራቸውን አብራርተዋል።

ይህም የተሻለ ሕክምና ፍለጋ ወደ ውጭ ሀገር የሚሄዱ ዜጎችን ቁጥር ትርጉም ባለው መልኩ መቀነስ ያስቻለ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ኢትዮጵያን የጤና ቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ የተያዘውን ግብ ውጤታማ ለማድረግ በአዲስ አበባ እና በክልል ከተሞች በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ ትላልቅ ሆስፒታሎች ተገንብተው ወደ ስራ መግባታቸውን አመልክተዋል፡፡

በሌላ በኩል መድኃኒትና የሕክምና መሣሪያዎችን በሀገር ውስጥ አቅም ማምረት ለዘርፉ ዘላቂ ስኬት ቁልፍ ጉዳይ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታው÷ በዚህም መንግሥት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ በመንቀሳቀሱ በርካታ አበረታች ውጤቶች እየተመዘገቡ እንደሚገኝ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.