Fana: At a Speed of Life!

ምርጫው የክልሉ ሕዝብ ለዴሞክራሲና ሰላማዊ ፖለቲካ ያለው ፍላጎት የታየበት ነው

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 27፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሕዝቡ ለዴሞክራሲና ሰላማዊ ፖለቲካ ያለውን ጽኑ ፍላጎት ያሳየበት ነው አለ የጋምቤላ ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ም/ቤት፡፡

በጋምቤላ ክልል ሕዝቡ ያለምንም ችግር በሰላማዊ መንገድ ድምጽ መስጠቱን የጋራ ምክር ቤቱ አስታውቋል፡፡

የጋራ ምክር ቤቱ ሰብሳቢ ኮማንደር ጋትቤል ቦል ምርጫው ከዝግጅት ጀምሮ የተሻለ ቅንጅት የታየበት እንደነበር ጠቅሰው፥ ም/ቤቱ ለምርጫው ስኬት አስተዋፅኦ ማድረጉን አንስተዋል።

ምርጫው ያለምንም የጸጥታ ችግር በሰላም መጠናቀቁ ለዴሞክራሲያዊ ሒደቱ ትልቅ ስኬት ነው ያሉት ሰብሳቢው፥ ሕብረተሰቡ ከማለዳ ጀምሮ እስከ እኩለ ሌሊት ድረስ በትዕግስትና በጽናት ድምጹን ለመስጠት ያሳየውን ተሳትፎ አድንቀዋል፡፡

ይህም ሕዝቡ ለዴሞክራሲና ለሰላማዊ ፖለቲካ ያለውን ፍላጎት የሚያንጸባርቅና የዲሞክራሲ ባህል እያደገ መምጣቱን የሚያመላክት መሆኑን የጋራ ምክር ቤቱ ገልጿል፡፡

ሁሉም ባለድርሻ አካላት ባደረጉት የጋራ ጥረት ሕዝቡ የፈለገውን ፓርቲና እጩ በነፃነት የመምረጥ መብቱን እንዲጠቀም ማስቻሉንም አመልክቷል፡፡

በዚህ ምርጫ ሒደት በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የታየው የትብብር ባህል ወደፊትም ሊቀጥል እንደሚገባ በመግለጽ የሕዝብ ድምፅ ሁሌም መከበር እንዳለበት አስገንዝቧል፡፡

በክልሉ ምርጫው በሰላም እንዲጠናቀቅ የበኩላቸውን ሚና ለተወጡ አካላት የጋራ ምክር ቤቱ ምስጋና አቅርቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.