Fana: At a Speed of Life!

በአንድ ጀምበር የተጻፈ የኢትዮጵያውያን የዴሞክራሲ ታሪክ አሻራ…

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 28፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በዓለም የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ በአንድ ጀምበር በሚሊየኖች የሚቆጠሩ መራጮችን አስተናግዶ ምርጫን በስኬት ማጠናቀቅ እጅግ ፈታኝና ጠንካራ ተቋማዊ አቅምን የሚጠይቅ ግዙፍ ክዋኔ ነው።

በዓለም ላይ በአንድ ቀን ውስጥ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ ድምጽ የሚሰጥበት ታሪካዊ ክስተት ሲነሳ፥ ኢንዶኔዢያ በአንድ ቀን ከ200 ሚሊየን በላይ መራጮችን በማሳተፍ ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ናት።

እንደ ሕንድ እና አሜሪካ ያሉ ሀገራት በ100 ሚሊየኖች የሚቆጠሩ መራጮች ቢኖሯቸውም፥ የምርጫ ሥርዓታቸው በየደረጃውና በረጅም ቀናት ሒደት የሚጠናቀቅ በመሆኑ በዚህ የታሪክ ጎራ ውስጥ አይመደቡም።

ኢትዮጵያም ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም በአንድ ቀን ውስጥ ከ54 ሚሊየን በላይ መራጮችን በይፋ በማስተናገድ በዓለም ግዙፍ የአንድ ቀን ምርጫዎች ካካሄዱ ሀገራት መካከል መሆን ችላለች።

በዚህ ታሪካዊ ክስተት ላይ የታየው ትልቁ ስኬት ኢትዮጵያ ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ ገለልተኛና ነጻ የሆኑ ተቋማትን ለመገንባት ያደረገችው የሪፎርም ሥራ ፍሬ ሲሆን፥ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የዚህ ተቋማዊ ሽግግር ዋነኛ ማሳያ ሆኗል።

ቦርዱ ገለልተኛና በአሠራር ግልጽነት ላይ የተመሠረተ መዋቅር መገንባቱ፣ ከ10 ሺህ በላይ የሚሆኑ የፖለቲካ ፓርቲ ዕጩዎች እና 80 የግል ዕጩዎች የተሳተፉበትን ሰፊ ፉክክር ያለ ምንም መስተጓጎል በገለልተኝነት እንዲመራ አስችሎታል።

ይህ ተቋማዊ ጥንካሬ በምርጫው ማግስት ዓለም አቀፋዊ ዕውቅናን እንዲያገኝ ማስቻሉ የሥራውን ቅቡልነት ይበልጥ ያጠናክራል፡፡

የአውሮፓ ኅብረት አባል ሀገራት እንዲሁም የካናዳ፣ የኖርዌይ እና ስዊዘርላንድ ኤምባሲዎች በጋራ ባወጡት መግለጫ ቦርዱ ምርጫው በስኬት እንዲካሄድ ያደረገውን የላቀ አስተዋጽኦ በይፋ አድንቀዋል።

በምርጫ ሒደቱ ላይ የዲጂታላይዜሽን ትግበራው ለዚህ ስኬት ሌላው መሠረታዊ ምሰሶ ከሆኑ ጉዳዮች መካከል ተጠቃሽ ነው፡፡

በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የመራጮች ምዝገባን ጨምሮ የሎጂስቲክስ ቁጥጥር ሥርዓቶች በቴክኖሎጂ የታገዙ መሆናቸው ትልቅ ሚና ተጫውቷል።

ከ250 ሺህ በላይ የተፎካካሪ ፓርቲ ተወካዮች እንዲሁም በኬንያ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ የተመራው ባለ 59 አባላቱ የአፍሪካ ሕብረት እና ባለ 26 አባላቱ የኢጋድ ታዛቢ ቡድኖች ሒደቱን የታዘቡት ሲሆን÷ ይህም የሒደቱን ዴሞክራሲያዊነትና ተአማኒነት ይበልጥ ያጎላ ነው።

ታዛቢዎቹ የምርጫ ሒደቱ አካታች፣ አሳታፊና ፍትሃዊ ከመሆኑ ባለፈ ኢትዮጵያውያን ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ያላቸውን ቀናኢነት እና ቁርጠኛነት ያሳዩበት መሆኑን በሪፖርታቸው አስገንዝበዋል፡፡

በአጠቃላይ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ኢትዮጵያ በአንድ ቀን ውስጥ በሚሊየን የሚቆጠር ሕዝብን በሰላምና በሥርዓት የማስተናገድ ከፍተኛ የተቋም ብቃት የገነባችበት እና በዴሞክራሲ ጉዞዋ ላይ አዲስ ታሪካዊ ምዕራፍ የከፈተችበት ታላቅ ክስተት ሆኖ ተካሂዷል፤ በዚህ ሒደትም ኢትዮጵያ አሸንፋለች።

በዮናስ ጌትነት

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.