Fana: At a Speed of Life!

የአማራ ክልል የሚሊሻ ኃይል የሰላም ዘብ ሆኖ ያገለገለ የሀገር ባለውለታ ነው – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 29፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ የአማራ ክልል የሚሊሻ ኃይል በሰላም ጊዜ የልማት ኃይል በችግር ጊዜ የሰላም ዘብ ሆኖ ያገለገለ የሀገር ባለውለታ ነው አሉ።

የአማራ ክልል ሚሊሻ የ30ኛ ዓመት የምስረታ በዓል አከባበርና የእውቅና መርሐ ግብር በዛሬው ዕለት ተካሂዷል፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመድረኩ ባስተላለፉት መልዕክት፥ በዓሉን የምናከብረው ሕዝብ፣ የፖለቲካ አመራሮችና የጸጥታ አካላት በቅንጅት ታሪክ በሠሩበት በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ወቅት ላይ ነው ብለዋል።

ምርጫው ሰላማዊ እንዲሆን የአማራ ክልል ሚሊሻ ከፌዴራልና ከክልሉ የጸጥታ አካላት ጋር ያደረገውን አስተዋጽኦ ታሪክ ምንጊዜም ሲያስታውሰው ይኖራል ሲሉም ተናግረዋል።

ላለፉት ሦስት አስርት ዓመታት የሕዝብ ልጅ የሆነው የሚሊሻና ሰላም አስከባሪ ኃይል፣ ሀገርና ክልል በገጠሟቸው ፈተናዎች ሁሉ ግንባር ቀደም በመሆን መሰለፉን አውስተዋል፡፡

የምስረታ በዓሉ በሚሊየን የሚቆጠሩ ጀግኖችን የ30 ዓመታት የጽናት፣ የጀግንነት፣ የታማኝነትና የሕዝባዊነት ታሪክን ጭምር የምንዘክርበት ነው ብለዋል።

የሚሊሻ ኃይሉን ልዩ የሚያደርገው ከማኅበረሰቡ የወጣ፣ ከሕዝብ ጋር አብሮ የሚያርስ እንዲሁም የሀገርና የሕዝብ ጥሪ ሲመጣ ማረሻውንና መዶሻውን ለቀሪው አስረክቦ ወደ ግንባር የሚተምም የቁርጥ ቀን ኃይል በመሆኑ ነው ሲሉም አመልክተዋል።

የውስጥና የውጭ የትርምስ ኃይሎች የሕዝባችንን ሰላም ለመንሣት በሚጥሩበት በዚህ ወቅት የሚሊሻ ኃይል ዝግጁነትና ንቃት ከምንጊዜውም በላይ ያስፈልጋል በማለት አጽንኦት ሰጥተዋል።

መንግሥት የሚሊሻውን ኃይል አደረጃጀት ዘመናዊ ለማድረግ፣ በዕውቀትና በሥልጠና ለማጠናከር እንዲሁም ትጥቅና አቅርቦቱን ለማሻሻል የጀመረውን ተቋማዊ የሪፎርም ሥራ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ጠቁመዋል።

በተጨማሪም የሚሊሻ አባላትና ቤተሰቦቻቸው የሚገባቸውን ክብርና ድጋፍ እንዲያገኙ በትኩረት ይሰራል ነው ያሉት፡፡

ለሀገራችሁና ለሕዝባችሁ ስትሉ ለከፈላችሁት መሥዋዕትነት ሁሉ በመንግሥትና በራሴ ስም ላቅ ያለ ምስጋናዬን አቀርባለሁ ብለዋል።

በለይኩን ዓለም

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.