በትናንት ጉዳይ ላይ መነታረክ ነገን ያበላሻል – አምባሳደር ቴዎድሮስ ግርማ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 3፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በትናንት ጉዳይ ላይ መነታረክ ዛሬን ብቻ ሳይሆን ነገም እንዲበላሽ ያደርጋል አሉ በካናዳ የኢትዮጵያ አምባሳደር ቴዎድሮስ ግርማ።
ለሀገር አንድነት ፈተና ከሚሆኑ ችግሮች መካከል በታሪክ አጋጣሚ የሚፈጠሩ መቃረኖች እና አለመግባባቶችን በውይይት አለመፍታት አንዱ ሲሆን÷ በኢትዮጵያ ለዘመናት የቆዩ ችግሮችን ለማስተካከል ያለመው ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአሁኑ ወቅት ወደ መጨረሻው ምዕራፍ ተቃርቧል።
ከፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር ቆይታ ያደረጉት አምባሳደር ቴዎድሮስ ግርማ እንዳሉት÷ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ የደረሰበት ደረጃ ያለፉትን ስኬታማ ጉዞዎች የሚያሳይ ነው።
ካናዳ አጋጥመዋት የነበሩ የቀውስ እና የበደል ታሪኮችን ለመቀየር የእውነትና እርቅ ማስፈን ሂደት በማካሄድ ወደፊት መራመድ መቻሏን በምሳሌነት አንስተዋል።
ስለሆነም ትርጉም በሌላቸውና ትናንትን በሚያበላሹ አጀንዳዎች ላይ ከመጓተት ይልቅ በመነጋገር፣ ችግሮችን ነቅሶ በማውጣትና በማረም ሀገር መገንባት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ከዚህ አንጻር ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ እስካሁን ነጻነቱን ጠብቆ የሰራው ሥራ አስደናቂ እንደሆነ ተናግረዋል።
በካናዳ በተዘጋጀው መድረክ ላይ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ኢትዮጵያውያን ተሳትፈው ገንቢ ውይይት መደረጉንም አንስተዋል።
በካናዳ የሚኖሩት ኢትዮጵያዊ አቶ መልካ ለገሰ በበኩላቸው÷ ሀገር መመራት ያለበት በሀገር ውስጥ ባለው በኢትዮጵያዊ ሃሳብ መሆን እንደሚገባው ገልጸዋል።
ቀደም ሲል ዳያስፖራው የፖለቲካ ሃሳብን በራሱ በመምራት ኢትዮጵያን ወደ ልማት ለማምጣት ያደረገው ሙከራ ትክክል እና አዋጭ እንዳልነበር ጠቁመው÷ ይህ መንገድ መደገም እንደሌለበት አስገንዝበዋል።
በውጭ ሀገራት የሚኖረው ኢትዮጵያዊ ሚና ገንቢ ሃሳቦችን ማቅረብና ሀገርን መደገፍ ብቻ መሆን እንዳለበት አመልክተዋል።
በዮናስ ጌትነት