Fana: At a Speed of Life!

የ2019 በጀት ዓመት ረቂቅ በጀት 2 ነጥብ 339 ትሪሊየን ብር ሆኖ ቀረበ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 4፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት 2 ነጥብ 339 ትሪሊየን ብር ሆኖ በቀረበው የ2019 በጀት ዓመት ረቂቅ በጀት ላይ እየመከረ ነው፡፡

የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሺዴ የረቂቅ በጀቱን መግለጫ ለምክር ቤቱ ባቀረቡበት ወቅት እንዳሉት፥ በጀቱ መንግስት የያዛቸውን የልማትና የማክሮ ኢኮኖሚ እቅዶች ታሳቢ በማድረግ የተዘጋጀ ነው፡፡

ለ2019 በጀት ዓመት ከቀረበው በጀት ውስጥ 1 ነጥብ 236 ትሪሊየን ብር ለመደበኛ ወጪ፣ 568 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር ለካፒታል ወጪ እንደሚውል አስረድተዋል፡፡

በተጨማሪም 520 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር ለብሔራዊ ክልላዊ መንግስታት የበጀት ድጋፍ እንዲሁም 14 ቢሊየን ብር ለክልሎች የዘላቂ ልማት ግብ ማስፈጸሚያ ይውላል ነው ያሉት፡፡

ከአጠቃላይ በጀቱ ውስጥ 52 ነጥብ 9 በመቶ የሚሆነው ከፍተኛ በጀት ለመደበኛ ወጪ የተመደበ መሆኑን ገልጸው፥ ከዚህም ውስጥ 542 ቢሊየን ብር ለሀገር ውስጥ እና ለውጭ የእዳ ክፍያ እንደሚውል ጠቁመዋል፡፡

በተጨማሪም ከዚሁ የመደበኛ ወጪ ውስጥ 236 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር ለማዳበሪያ፣ ለነዳጅ ድጎማ እንዲሁም የኢትዮጵያ ነዳጅ ድርጅትን ካፒታል ለማሳደግ የተመደበ ነው ብለዋል፡፡

ለመንግስት ባለበጀት መስሪያ ቤቶች ለደመወዝ፣ ለአበልና ልዩ ልዩ ክፍያዎች 170 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር መመደቡን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በ2019 በጀት ዓመት 10 ነጥብ 1 በመቶ እድገት እንደሚያስመዘግብ ይጠበቃል ነው ያሉት፡፡

የመካከለኛው ምስራቅ ጦርነት በኢኮኖሚ እድገቱ ላይ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር አመላካች ሁኔታዎች መኖራቸውን ገልጸው፥ የ2019 በጀት ጦርነቱ የሚያሳድረውን ተጽእኖ ከግምት በማስገባት መዘጋጀቱን አስረድተዋል፡፡

በ2019 በጀት ዓመት የፌደራል መንግስት ጠቅላላ ገቢ 1 ነጥብ 817 ትሪሊየን ብር እንደሚሆን ግምት ተወስዷል ያሉት ሚኒስትሩ፥ ከዚህም ውስጥ 1 ነጥብ 6 ትሪሊየን ብር ከታክስና ታክስ ካልሆኑ ገቢዎች እንደሚሰበሰብ መታቀዱን አመልክተዋል፡፡

ለ2019 በጀት ዓመት የቀረበው 2 ነጥብ 339 ትሪሊየን ብር በጀት ከዘንድሮው በጀት ዓመት አንጻር የ21 ነጥብ 3 በመቶ እድገት እንዳለው ተናግረዋል፡፡

በኃይለማርያም ተገኝ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.