Fana: At a Speed of Life!

የቀድሞ ሕወሓት በትግራይ ክልል የሚከናወኑ የዘላቂ ሰላምና ልማት ግንባታ ጥረቶችን እያደናቀፈ ነው – አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 8፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የፌደራል መንግሥት የትግራይን ዘላቂ ሰላምና ልማት ለማስቀጠል የወሰደውን ቁርጠኝነት የቀድሞ ሕወሓት ራሱን ለዕኩይ ዓላማ ለማደራጀት ተጠቅሞበታል አሉ አረጋዊ በርሔ (ዶ/ር)፡፡

የቀድሞው ሕወሓት ሊቀ መንበር የነበሩት አረጋዊ በርሔ (ዶ/ር) እንዳሉት፥ የፌደራል መንግሥት ከፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ማግስት የክልሉን ጊዜያዊ አስተዳደር በማዋቀር ሰብዓዊ ድጋፍና መልሶ ግንባታን ለማፋጠን ከፍተኛ በጀት መድቦ ሲሰራ ቆይቷል።

ሆኖም ጦርነት ናፋቂው የቀድሞ ሕወሓት ፅንፈኛ ቡድን ስምምነቱን ለጥፋት ዓላማው ጊዜ መግዣነት በመጠቀም አደገኛና ህገወጥ ወታደራዊ አቅም እየገነባ መቀጠሉን አመልክተዋል።

በዚህም የዘላቂ ሰላምና ልማት ግንባታ ጥረቶች እንዳይሳኩ ተደጋጋሚ የማደናቀፍ ተግባራትን እየፈጸመ መሆኑን አስረድተዋል።

የቡድኑ አመራሮች ከውጪ ጠላት በሚሰጣቸው ትዕዛዝ መሰረት ሕጻናትን ከወላጆቻቸው በመንጠቅ ጭምር አዲስ ኃይል አደራጅተው ወደ ዳግም ግጭት ለመግባት የተሳሳተ አቅጣጫ እየተከተሉ ነው ብለዋል፡፡

የትግራይ ክልል ወጣቶችን ለአስገዳጅ ወታደራዊ አፈሳና ምልመላ በመዳረግ ስጋት እንዲያንዣብብ ማድረጉን ገልጸው፥ የክልሉ ሕዝብ የቡድኑን ሕገወጥ ድርጊት አጥብቆ እየተቃወመ ይገኛል ነው ያሉት፡፡

በዚህ ፅንፈኛ ቡድን በመሰላቸት ተስፋ የቆረጡ ነባር ታጣቂዎችም ለቀው በመውጣት ቡድኑን መዋጋት ጀምረዋል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በሀገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩ የትግራይ ክልል ተወላጆችና ሌሎች ኢትዮጵያውያን እንዲሁም ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የፅንፈኛ ቡድኑን ሕገወጥ እንቅስቃሴ አጥብቀው ሊያወግዙ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.