በመዲናዋ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት የተከናወኑ ዘርፈ ብዙ ሥራዎች…
በጎ ፈቃደኝነት ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና አካባቢያዊ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል የሰብዓዊነት ተግባር ነው፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ የክረምትና የበጋ ወራት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ፕሮግራሞች ተቀርጸው በጎ ፍቃደኛ፣ ባለሃብቶች፣ ወጣቶችንና የከተማዋን ነዋሪዎች ማሳተፍ ተችሏል፡፡
በጎ ፈቃደኞች ጉልበታቸውን፣ ገንዘባቸውን፣ ጊዜያቸውንና እውቀታቸውን እንዲያበረክቱ ለማድረግ ለማሕበረሰቡ በተደራጀ መንገድ የተለያዩ የሰብዓዊነት አገልግሎቶች በመሰጠት ይገኛሉ፡፡
በጎ ፈቃደኝነት በተፈጥሮና በሰው ሰራሽ ሁኔታ በሚፈጠር ችግር፣ በፈተና እና በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ግንባር ቀደሞ ደራሽ መሆን ነው፡፡
ባለፉት ዓመታት በአዲስ አበባ ተቀርፀው በተከናወኑ ከ15 በላይ ዋና ዋና አሳታፊ የበጎ ፈቃድ መርሐ ግብሮች፣ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ባህልና ተደራሽነት በከፍተኛ ደረጃ እያደገ መጥቷል።
በእነዚህ የበጎ ፈቃድ ተግባራት ከ55 ነጥብ7 ቢሊየን ብር በላይ የበጎ ፍቃድ ተግባራት ተከናውነዋል፡፡
በየዓመቱ በአማካይ ከ2 ነጥብ 6 ሚሊየን በላይ በጎ ፈቃደኞችን በማሳተፍ በድግግሞሽ 9 ነጥብ 3 ሚሊየን የሚሆኑ የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል፡፡
በመዲናዋ ከተከናወኑ መጠነ ሰፊ የበጎ ፈቃድ ሥራዎች መካከልም በቤት ግንባታ መርሐ ግብር 46 ሺህ 441 ቤቶች ተገንብተው ለአቅመ ደካሞችና ለሀገር ባለውለታዎች ተላልፈዋል። በድግግሞሽ 6 ነጥብ 1 ሚሊየን የሚሆኑ ዜጎች ማዕድ ተጋርተዋል፡፡
በህፃናት ድጋፍ መርሐ ግብር ወላጆቻቸውን ያጡ 2 ሺህ 351 ህፃናት የልዩ ድጋፍ ተጠቃሚ ሆነዋል። ከፍለው መታከም የማይችሉ 525 ሺህ 531 ወገኖች ደግሞ ነጻ የህክምና አገልግሎት አገኝተዋል፡፡
354 ሺህ 938 ዩኒት ደም በበጎ ፈቃደኞች የተለገሰ ሲሆን ÷ ለ632 ሺህ497 ተማሪዎች የማጠናከሪያ ትምህርትና የስልጠና ድጋፍ ተደራሽ ሆኗል።
በየዓመቱ ከ20 ሺህ በላይ በጎ ፈቃደኞች በመንገድ ትራፊክ ደህንነት፣ በሙያ በጎ ፈቃድ መርሐ ግብሮች ላይ መሳተፋቸውን የከንቲባ ጽ/ቤት መረጃ አመልክቷል፡፡
የበጎ ፈቃድ ፕሮግራም በከተማዋ የነበረውን የመረዳዳትና የመደጋገፍ እሴት ከማሳደጉ ባለፈ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ዜጎች አለኝታ መሆን የቻለ የሰብዓዊነት መርሐ ግብር ነው።