የግብርና ቢዝነስ ኩባንያ የግብርና ዘርፉን ወደ አዲስ ምዕራፍ የሚያሸጋግር ነው – አቶ አዲሱ አረጋ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 10፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የግብርና ሚኒስትር አዲሱ አረጋ የግብርና ቢዝነስ ኩባንያ ዘርፉን ወደ አዲስ ምዕራፍ ለማሸጋገር ትልቅ አቅም ይፈጥራል አሉ፡፡
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በግብርና ቢዝነስ ኩባንያ ረቂቅ አዋጅ ላይ የሕዝብና የባለድርሻ አካላት የውይይት መድረክ አካሂዷል፡፡
ሚኒስትሩ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ ረቂቅ አዋጁ አነስተኛ ይዞታ ያላቸውን አርሶ እና አርብቶ አደሮች እንዲሁም ከፊል አርብቶ አደሮች በማደራጀት ተጠቃሚነታቸውን ያረጋግጣል፡፡
የኩታ ገጠም እርሻ ሽፋን አሁን ላይ 13 ሚሊየን ሄክታር መድረሱን ገልጸው፥ ረቂቅ አዋጁ የተገኘውን ተሞክሮ በማሳደግ አርሶና አርብቶ አደሮች ወደ ኢንቨስትመንት ኩባንያ እንዲሸጋገሩ ያስችላል ነው ያሉት፡፡
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ሰለሞን ላሌ በበኩላቸው፥ ግብርና የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዕድገት፣ የኢንዱስትሪ ልማትና የስራ ዕድል ፈጠራ ዋነኛ መሠረት በመሆኑ ከኋላቀር አሰራር በመላቀቅ ወደ ዘመናዊ፣ ተወዳዳሪና ገበያ መር ሥርዓት መሸጋገር እንደሚገባ ገልጸዋል።
ረቂቅ አዋጁ አርሶና አርብቶ አደሮችን እንዲሁም ከፊል አርብቶ አደሮችን በኩባንያ በማደራጀት መሬት የመጠቀም መብታቸውን፣ የእንስሳት ሀብታቸውንና ጉልበታቸውን ወደ ካፒታል በመለወጥ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ ያስችላል ብለዋል፡፡
ምክር ቤቱ ባካሄደው 23ኛ መደበኛ ስብሰባው ረቂቅ አዋጁን ለዝርዝር እይታ ለግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መምራቱ ይታወሳል፡፡