ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) የዘንድሮውን የክረምት በጎ ፈቃድ ዘመቻ በይፋ አስጀመሩ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 11፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀገራችንን በጋራ ማንሳት የምንችለው አንዳችን ለሌላችን እጃችንን ስንዘረጋ ብቻ ነው አሉ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን ጎሮ ወረዳ የዘንድሮውን የክረምት የበጎ ፈቃድ ዘመቻ በዛሬው ዕለት በይፋ አስጀምረዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት÷ የክረምቱ ወቅት ሲደርስ፣ እኛም ለወገኖቻችን የምንዘረጋው የደግነት እጅ አብሮ ይጀግናል ብለዋል፡፡
በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን፣ ጎሮ ወረዳ የዘንድሮውን የክረምት የበጎ ፈቃድ ዘመቻ ማስጀመራቸውን ነው የገለጹት፡፡
የገጠር ኮሪደር ልማት መርሐ ግብር አካል በሆነው ዲዛይን መሠረት 20 ቤቶች በአካባቢው እንደሚገነቡም አብራርተዋል፡፡
ሀገራችንን በጋራ ማንሳት የምንችለው አንዳችን ለሌላችን እጃችንን ስንዘረጋ ብቻ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በዚህ ሥራ እንዲሳተፍ ጥሪ አቅርበዋል፡፡