እውነተኛ ብልጽግና የሚመጣው የዜጎችን ጉልበት፣ ሃብትና እውቀት ደምሮ መጠቀም ሲቻል ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 11፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እውነተኛ ብልጽግና የሚመጣው የኢትዮጵያ ትልቅ ሃብት የሆኑት ከ130 ሚሊየን በላይ ዜጎች ጉልበታቸውን፣ሀብታቸውንና እውቀታቸውን ሲደምሩ ነው አሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን ጎሮ ወረዳ የዘንድሮውን የክረምት የበጎ ፈቃድ ዘመቻ በዛሬው ዕለት በይፋ አስጀምረዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት÷ የክረምት በጎ ፈቃድ ሥራዎቻችን ላለፉት ጥቂት ዓመታት ብዙ ውጤት አስገኝተዋል ብለዋል።
መንግሥት ባለው በጀት እና የገንዘብ አቅም ብቻ ሊረጋገጥ የሚችል ዘላቂ ብልጽግና እንደሌለም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
እውነተኛ ብልጽግና የሚመጣው ትልቁ የሀገሪቱ ሃብት የሆኑት ከ130 ሚሊየን በላይ ዜጎች ጉልበታቸውን፣ ሀብታቸውንና እውቀታቸውን ሲደምሩ መሆኑን አስገንዝበዋል።
ለዚህም በማሳያነት ባለፉት አምስትና ስድስት ዓመታት ውስጥ በማሕበረሰብ ተሳትፎ የተገነቡትን 35 ሺህ መዋለ ሕጻናት በምሳሌነት አንስተዋል።
ይህንን ሰፊ ግንባታ መንግሥት ብቻውን አቅዶ ለመስራት ቢሞክር የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የአፍሪካ መንግሥታትም ቢሆኑ ዓመታት ሊፈጅባቸው እንደሚችል አመልክተዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በዚህ ሀገር በቀል አቅም ከ4 ሚሊየን በላይ ሕጻናት በመዋለ ሕጻናት ታቅፈው የመማር ዕድል ማግኘታቸውን ነው ያብራሩት፡፡
በጎ ፈቃድ በዋናነት የአቅመ ደካሞችንና የዕለት እጅ አጠር ሰዎችን መኖሪያ ቤቶች የመጠገንና የመገንባት ሥራዎችን ያካተተ ነው ብለዋል።
በተጨማሪም የሀገር በቀልና የፍራፍሬ ችግኞችን በመትከል እንዲሁም በአንዳንድ አካባቢዎች የባህር ዛፎችን በመቀነስ ረገድ የሚከናወኑት የአካባቢ ጥበቃ ተግባራት የዚሁ በጎ ፈቃድ አገልግሎት ዋነኛ አካል መሆናቸውን አስረድተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ ከበጀት ውጪ የሆኑና የማሕበረሰቡን የዕለት ተዕለት ችግሮች የሚፈቱ በርካታ ውጤታማ ሥራዎች መከናወናቸውን አንስተዋል።
ከእነዚህም መካከል ቀበሌዎችንና ሰፈሮችን የሚያገናኙ የገጠር መንገዶች፣ መለስተኛ ድልድዮች፣ ፋርማሲዎችና የመዋለ ሕጻናት ግንባታዎች ይጠቀሳሉ።
ዘንድሮም ልክ ባለፈው ዓመት በማዕከላዊ ኢትዮጵያ እንደተከናወነው ሁሉ፣ በወሊሶ ከተማ መጠነኛ የመኖሪያ ቤቶችን የመገንባት ሥራ መጀመሩን ጠቁመዋል።
ባለፈው ዓመት በወልቂጤ፣ በስልጤ ወራቤ፣ በሀዲያና በከምባታ የተጀመሩት የልማት ሥራዎች በየደረጃው ባሉ የአስተዳደር መዋቅሮችና በሕዝብ ተሳትፎ እያደጉና ተጨባጭ ውጤት እያመጡ መሆናቸውን አስታውሰዋል።
በቀጣይም በሁሉም ክልሎች፣ ዞኖችና ወረዳዎች የሚገኘው ማሕበረሰብ ተባብሮ ቤቶችን፣ ትምህርት ቤቶችን፣ መንገዶችን፣ ድልድዮችን፣ ፋርማሲዎችንና የጤና ኬላዎችን እንደሚገነባ አመልክተዋል።
እነዚህ በአካባቢ አቅም የሚከናወኑ ተግባራት መንግሥት በበጀትና በእቅድ ከሚሠራቸው ጋር ተሰናስለው ሲደመሩ የኢትዮጵያን ብልጽግና እንደሚያረጋግጡም አጽንኦት ሰጥተዋል።
በሶስና አለማየሁ