Fana: At a Speed of Life!

በክልሉ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት 3 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር የሚገመት ወጪን ለማዳን..

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 12፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከ3 ነጥብ 5 ሚሊየን በላይ የሚሆኑ ዜጎች በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ይሳተፋሉ አለ የክልሉ ወጣቶች ጉዳይና በጎ ፈቃድ አገልግሎት ኮሚሽን ።

የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ማርቆስ ማቲዮስ ለኢዜአ እንዳሉት÷ ቀደም ሲል በበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ ወጣቶች ብቻ ሲሳተፉ ቆይተዋል።

በአሁኑ ጊዜ ግን የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች እንደሚሳተፉበት ጠቁመው÷ በዘንድሮው የክረምት ወራት 19 የስራ መስኮች ስር ባሉ ተግባራት ላይ ትኩረት ያደረገ ስራ እንደሚከናወን ተናግረዋል።

የገጠር ኮሪደር ልማት፣ የአረጋውያን ቤት እድሳት፣ የደም ልገሳ፣ አረንጓዴ አሻራ፣ ትምህርት፣ ጤናና የአካባቢ ጥበቃ ስራዎች ከተለዩ የትኩረት መስኮች ዋነኞቹ ናቸው።

በተለይም በዘንድሮ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የህዝብ ለህዝብ ትስስርን፣ አብሮነትን እና አንድነትን የሚያጠናክሩ ወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶችም ትኩረት ተሰጥቷቸዋል ነው ያሉት፡፡

በዚህም በክልሉ በዘንድሮ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ3 ነጥብ 5 ሚሊየን በላይ ዜጎችን ተሳታፊ የሚያደርጉ ተግባራት ይከናወናሉ ብለዋል።

በአገልግሎቱ ከ3 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር በላይ የሚገመት የመንግሥት እና የሕዝብ ወጪን ለማዳን እንደሚሰራም ኮሚሽነሩ ጠቁመዋል።

የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች በዘንድሮ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት በመሳተፍ አሻራቸውን እንዲያኖሩም ጥሪ አቅርበዋል ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.