Fana: At a Speed of Life!

አዲስ አበባ በአረንጓዴ ልማት ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ በሚያደርጋት መስመር ላይ ናት – አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 14፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአዲስ አበባ የተከናወኑ የአረንጓዴ ልማት ሥራዎች ከተማዋ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ የሚያደርጋትን መስመር እንድትይዝ አስችለዋል አሉ የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የ2018 ዓ.ም አረንጓዴ ዐሻራ የማስጀመሪያ መርሐ ግብር ‘‘ተስፋን እንትከል’’ በሚል መሪ ሀሳብ በዛሬው ዕለት ተካሂዷል፡፡

አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ እንደ ሀገር በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር የተከናወኑ ሥራዎች ከአካባቢ ጥበቃ ባለፈ ለዘላቂ ልማት አይተኬ ሚና እያበረከቱ ነው፡፡

ሀገራዊ ንቅናቄው በተቋም ደረጃ በተቀናጀ ሁኔታ እየተሰራ መሆኑ ሥራውን ይበልጥ ውጤታማ እንዳደረገው ጠቅሰው፥ በዚህም ዓለም አቀፍ እውቅና መገኘቱን አስታውሰዋል፡፡

በዚሁ የአረንጓዴ ልማትና ውበት ሥራ አማካኝነት አዲስ አበባ በአፍሪካ ደረጃ በምሳሌነት የምትጠቀስ ከተማ እየሆነች መምጣቷን አውስተዋል፡፡

ከተማዋ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ በሚያደርጋት መስመር እየተጓዘች ነው ያሉት አፈ ጉባኤው፥ በተለይም በአረንጓዴ ልማት የተገኘውን ውጤት አጠናክሮ ለማስቀጠል በላቀ ትኩረት መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

ሁሉም ዜጋ የተጀመረውን የአረንጓዴ አሻራ ንቅናቄ በላቀ ተነሳሽነት በመቀላቀል ለሀገር ዘላቂ ልማት የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ጥሪ አቅርበዋል።

በይስማው አደራው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.