በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ተጀመረ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 16፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የ2018 የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት በሀላባ ቁሊቶ ከተማ በይፋ ተጀምሯል።
በማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ ላይ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድ እንዳሻው ጣሰውን (ዶ/ር) ጨምሮ ከፍተኛ የሰራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) በውቅቱ እንዳሉት፥ በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት አማካኝነት ባለፉት ዓመታት የብዙ ወገኖችን እንባ ማበስ ተችሏል።
አሁንም ወገኖችን ተጠቃሚ ለማድረግ በዚህ ተግባር ብዙ መጓዝ እንደሚገባ አመልክተዋል።
በክልሉ በዓመት አንዴ ብቻ ያመርቱ የነበሩ አርሶአደሮች በዓመት ሁለትና ከዚያ በላይ እንዲያመርቱ የተሰሩ ስራዎች ውጤት ማምጣቸውን ጠቅሰዋል።
አክለውም ወደ ኢንዱስትሪ ለሚደረገው ሽግግር ገና ብዙ የቤት ሥራዎች እንዳሉ አንስተው፤ የኢትዮጵያን ብልጽግና ለማረጋገጥ ሕዝባችን አምኖ ለሰጠን ተጨማሪ ጊዜ ታምነን ሌት ተቀን እንሠራለን ነው ያሉት።
የክልሉ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ ጌታቸው ሌሊሾ እንደገለጹት፤ “በጎነት ለኢትዮጵያ ከፍታ” በሚል መሪ ቃል በሚካሄደው የዘንድሮ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ህብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተግባራት ይከናወናሉ።
በዚህም የከተሞች ፅዳት፣ የአቅመ ደካማ ቤቶች ዕድሳትና ግንባታ፣ ደም ልገሳ፣ የአረንጓዴ ዐሻራ ችግኝ ተከላን ጨምሮ የተለያዩ ተግባራት ይከናወናሉ ብለዋል።
በጎነት በኢትዮጵያ ውስጥ ቀድሞም የነበረ እሴት መሆኑን አስታውሰው፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ተቋማዊ መዋቅር ተበጅቶለት መንቀሳቀሱ የተሻለ ውጤት እያስገኘ መሆኑን አብራርተዋል።
ባለፉት ዓመታት ብቻ በክልሉ ውስጥ ከ1 ሺህ 600 በላይ የአቅመ ደካሞች ቤቶች በመታደሳቸውና በመገንባታቸው ብዙ ወገኖች ተጠቃሚ መሆን ችለዋል ብለዋል።
በበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ ወጣቶችን ጨምሮ በርካታ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፎ እንደሚያደርጉ ጠቁመዋል።
በጥላሁን ይልማ