በኮቪድ19 መከሰት የተቀዛቀዘው የህክምና አገልግሎት መሻሻል ማሳየቱ ተገለጸ
አዲስ አበባ ፣ ነሀሴ 24 ፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኮቪድ 19 መከሰት ተቀዛቅዞ የነበረው የመደበኛ፣የተላላፊና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች አገልግሎት መሻሻሉን ጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።
የኮሮና ተዋህሲ ወረርሺኝ በሀገራችን በተከሰተ የመጀመሪያዎቹ ወራት በጤና ተቋም የሚታከም የህብረተሰቡ ቁጥር መቀነሱን የጤና ባለሙያዎቹ ያስረዳሉ።
ይሄን ችግር ለመቅረፍም ጤና ሚኒስቴር የህክምና መስጫ ተቋማቱ ኮቪድ19ን ወረርሺኝን በመከላከልና ጥንቃቄን ማዕከል ያደረገ የመደበኛ የህክምና አገልግሎት እንዲሰጡ መመሪያ መተላለፉን በሚኒስቴሩ የበሽታዎች መከላከያና መቆጣጠሪያ ዳሬክቶሬት ዳሬክተር ወይዘሮ ሕይወት ሰለሞን አመልክተዋል።
ተቋማቱ መመሪያውን መሰረት በማድረግ እንደ ኤችአይ ቪ ኤድስና እና ሳንባ ለመሳሰሉት ተላላፊ በሽታዎች በትኩረት መሰራቱን ተናግረዋል።
በተለይም የመንግሥት የጤና ተቋማት የመደበኛ፣የተላላፊና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች አገልግሎት ከወረርሺኙ በፊት ወደነበረበት እየተመለሰ መሆኑን ዳሬክተሯ አስረድተዋል።
በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም የህክምና ኮሌጅ የህክምናው ዘርፍ ምክትል ፕሮቦስት ዶክተር ብርሃነፀሐይ ተክለወልድ ÷የኮቪድ 19 ወረርሺኝ መከሰትን ተከትሎ ሆስፒታሉ ከወሊድና አስቸኳይ ህክምና ውጪ ያሉ አግልጋሎቶችን ለተወሰነ ጊዜ ማቆሙን ያስታውሳሉ።
በአሁኑ ሰአት ሆስፒታሉ ለወረርሺኙ መከላከል ተገቢውን ጥንቃቄ በማድረግ የመደበኛ፣የተላላፊና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ህክምና መስጠቱን የሚገልጹት ዶክተር ብርሀነፀሐይ ኀብረተሰቡም ይሄን አውቆ ወደ ሆስፒታሉ እንዲመጣ ጥሪ አቅርበዋል።
ከዚያም ባለፈ የኮሮና ተዋሕሲ ህመምተኞችን የመንከባከብና አስተኝቶ የማከም አገልግሎት ከመደበኛ ህክምና ሕንፃውን ጭምር ለይቷል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
#FBC
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።