Fana: At a Speed of Life!

አዲስ አበባ ከመደበኛው ገበያ ከ15 እስከ 20 በመቶ በሚደርስ የዋጋ ቅናሽ ምርቶችን ለሸማቾች እያቀረበች ነው

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 8፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) አዲስ አበባ ከመደበኛው ገበያ ከ15 በመቶ እስከ 20 በመቶ በሚደርስ የዋጋ ቅናሽ፣ ምርቶችን ለሸማቾች ማቅረብ የቻሉ ግዙፍ የገበያ ማዕከላትን በመገንባት ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ ችላለች፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት፣ ሕገ ወጥ የደላላ ጣልቃ ገብነትን ለማስቀረት እና አምራቹን ከሸማቹ ጋር በቀጥታ ለማገናኘት 13 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር ወጪ አምስት ግዙፍና ዘመናዊ የተቀናጁ የገበያ ማዕከላት ተገንብተው አገልግሎት እየሰጡ ነው፡፡
የግብርና ምርቶች በተለይም አትክልትና ፍራፍሬ ሳይቆዩና ሳይበላሹ በቀጥታ ከእርሻ ቦታው ስለሚመጡ ኅብረተሰቡ የተሻለ ጥራቱን የጠበቀ ምርት ያገኛል፡፡
እነዚህ ማዕከላት በከተማዋ አራቱም አቅጣጫዎች መግቢያና መውጫ በሮች ላይ ስትራቴጂካዊ በሆነ መንገድ የተደራጁ ናቸው።
እነዚህም ቁጥር አንድ እና ቁጥር ሁለት የላፍቶ ሁለገብ የገበያ ማዕከላት፣ የለሚ ኩራ፣ የአቃቂ ቃሊቲ እና የኮልፌ የግብርና ምርቶች የገበያ ማዕከል ናቸው፡፡
የላፍቶ ሁለገብ የገበያ ማዕከላት በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ የተገነቡ ሲሆኑ÷ ማዕከል ቁጥር ሁለት ዘመናዊ ሃይፐር ማርኬት ነው፡፡ ይህም ሁሉንም ዓይነት የግብርና እና የኢንዱስትሪ ምርቶች በአንድ ቦታ እያቀረበ ያለ ግዙፍ ማዕከል ነው።
የለሚ ኩራ የግብርና ምርቶች የገበያ ማዕከል በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ በአያት እና ሰሚት አካባቢዎች አቅራቢያ የተገነባ ነው፡፡ ማዕከሉ ከፍተኛ የክምችት አቅም መፍጠር የቻለ ሲሆን፣ ከቦታ ስፋት አንፃር እጅግ ግዙፉ ነው፡፡
ሰፋፊ የችርቻሮ ሕንፃዎችን፣ የአስተዳደር ህንፃዎችን እና የጅምላ መሸጫና ማከማቻ መጋዘኖችን አካትቷል፡፡በቅርቡም የተቀናጀ የከተማ ግብርና ማዕከል አገልግሎት መስጠት ጀምሯል፡፡
የአቃቂ ቃሊቲ የግብርና ምርቶች የገበያ ማዕከል በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ መግቢያ በር ላይ የሚገኝ ሲሆን÷ ማዕከሉ ከፍተኛ የሎጂስቲክስና የገበያ ትስስር መፍጠር ያስችላል፡፡
ከደቡብና ከምስራቅ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚገቡ የምግብና የሰብል ምርቶችን በቀጥታ በመቀበል ለከተማዋ ሥርጭት እና ለሀገር አቀፍ የሎጂስቲክስ ትስስር ትልቅ ሚና ይጫወታል።
የኮልፌ የግብርና ምርቶች የገበያ ማዕከል በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ በቤቴል አካባቢ ነው የተገነባው ፤ከምዕራብ የሃገሪቱ ክፍሎች የሚመጡ የግብርና ምርቶችን በከፍተኛ መጠን በማከማቸትና በተመጣጣኝ ዋጋ ለሸማች በማቅረብ ሰው ሰራሽ የምርት እጥረትን በመከላከል የገበያውን ሚዛን ለማስጠበቅ እየረዳ ይገኛል።
ማዕከላቱ ከመደበኛው ገበያ ከ15 በመቶ እስከ 20 በመቶ የሚደርስ የዋጋ ቅናሽ ለሸማቾች ያቀርባሉ። ይህ ሊሆን የቻለው ምርቶች በቀጥታ ከአምራች አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች እንዲሁም የህብረት ስራ ማህበራት ስለሚመጡ ነው።
ከተማ አስተዳደሩ ከአምስቱ የገበያ ማዕከላት በተጨማሪ በቅዳሜና እሁድ ገበያ እንዲሁም በበዓላት ባዛሮችና ኤግዚቢሽን የአቅርቦት ብዛት እና ከመደበኛው ገበያ ባነሰ ዋጋ ምርት መቅረብ እንዲችል በማድረግ ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ ችላለች፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.