ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ መስኮች ያሰለጠናቸውን 1 ሺህ 37 ተማሪዎች አስመረቀ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 20፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ በመጀመሪያ፣ በሁለተኛና በሦስተኛ ዲግሪ እንዲሁም በስፔሻሊቲ ፕሮግራሞች ያሰለጠናቸውን 1 ሺህ 37 ተማሪዎች በዛሬው ዕለት አስመርቋል።
በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የሰላም ሚኒስትርና መሐመድ እድሪስ ባስተላለፉት መልዕክት፥ ተመራቂዎች ለሀገር አለኝታነታቸውን የሚያሳይ ተግባር ማከናወን እንዳለባቸው አሳስበዋል።
በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ልምድና እውቀት አካብተው የሚመረቁ ወጣቶች የሀገር ብስራቶችና መጻኢ ዕድልን የሚወስኑ ተስፋዎች መሆናቸውን ገልጸዋል።
ተመራቂ ተማሪዎች ለፍትህ መረጋገጥ፣ ለግብርና መዘመንና ለጤና አገልግሎት መሳለጥ እውቀታቸውንና ልምዳቸውን ማበርከት እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።
በተለይም የቴክኖሎጂ ተመራቂዎች የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን በማሳደግ ረገድ ትርጉም ያለው ለውጥ የማምጣት አደራ እንዳለባቸው ነው የገለጹት፡፡
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ጉቼ ጉሌ (ዶ/ር) በበኩላቸው፥ ዩኒቨርሲቲው በምህንድስና፣ በቴክኖሎጂ፣ በግብርናና በጤና የትምህርት መስኮች በርካታ ተማሪዎችን ሲያሰለጥን መቆየቱን አንስተዋል፡፡
በተለይም የጤናውን ዘርፍ በዩኒቨርሲቲው የልህቀት ማዕከል ለማድረግ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲው በ2018 ዓ.ም የትምህርት ዘመን በተለያዩ ደረጃዎችና የትምህርት ዘርፎች ከ30 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ሲያስተምር መቆየቱንም ገልጸዋል።
በማህሌት ኡኩሞ