የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ውጤቶች
የአንድ ሀገር የኢኮኖሚ ዕድገት ዘላቂ እና አስተማማኝ ሊሆን የሚችለው ከሀገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ፣ ባህል እና ውስጣዊ አቅም ጋር የተጣጣመ ፖሊሲ ሲቀረፅ ብቻ ነው።
ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት ያጋጠሟትን መዋቅራዊ የኢኮኖሚ ፈተናዎች ለመፍታት እና የውጭ ምንዛሪ እጥረትን፣ የዋጋ ንረትን እንዲሁም የሥራ አጥነት ችግርን ለመቅረፍ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሃ ግብር ቀርጻ ወደ ተግባር ገብታለች።
ይህ ሪፎርም የሀገሪቱን የኢኮኖሚ ምሰሶዎች በማዘመን ረገድ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ይገኛል።
ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው በዋናነት ኢኮኖሚውን ከበጀት ጉድለት፣ ከከፍተኛ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ዕዳ ጫና፣ እንዲሁም ከገበያ መዛባት ማውጣት እየቻለ ነው፡፡
በሌላ በኩል የካፒታል ፍሰትን በማስተካከል፣ የውጭ ምንዛሪ አቅርቦትን በማሳደግ እና የፋይናንስ ዘርፉን በማዘመን ማክሮ-ኢኮኖሚያዊ መረጋጋትን ፈጥሯል፡፡
የመንግሥት የልማት ድርጅቶች አሠራርን በማሻሻል፣ የተንዛዛ ቢሮክራሲን በማስወገድ እና የንግድ ሥራ ምኅዳሩን በማስፋት መዋቅራዊ ማሻሻያ እንዲተገበርም አድርጓል፡፡
የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው እንደ ግብርና፣ ማኑፋክቸሪንግ፣ ማዕድን፣ ቱሪዝም እና የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ያሉትን ቁልፍ የኢኮኖሚ ዘርፎች ልማት ማፋጠን የቻለም ሆኗል፡፡
ሪፎርሙ የሀገሪቱን የኢኮኖሚ መዋቅር ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር አምስት ዋና ዋና ዘርፎችን እንደ ስትራቴጂክ ምሰሶዎች ለይቶ ተንቀሳቅሷል፡፡
የመጀመሪያው ዘመናዊ ግብርና ሲሆን፣ በዚህም የስንዴ ልማት ስኬትን አስመዝግቧል፡፡
ግብርናውን ከዝናብ ጥገኝነት በማውጣት በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ላይ የተመዘገበው ስኬት የሪፎርሙ ትልቁ ማሳያ ነው።
ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት የሀገር ውስጥ ፍላጎቷን ከመሸፈን አልፋ ስንዴን ወደ ውጭ ሀገራት የመላክ አቅም ፈጥራለች።
ማኑፋክቸሪንግ እና የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ሁለተኛው የማሻሻያው ምሰሶ ነው፡፡
በዚህ ዘርፍ የሀገር ውስጥ ምርቶችን ማበረታታት፣ የገቢ ምርቶችን በሀገር ውስጥ መተካት እና የግሉን ዘርፍ በኢንዱስትሪ ልማት ውስጥ በስፋት ለማሳተፍ በር ከፍቷል።
ሦስተኛው የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ምሰሶ ቱሪዝም እና የሀገር ገጽታ ግንባታ ነው፡፡
እንደ ገበታ ለሀገር እና ገበታ ለትውልድ ባሉ ታላላቅ ፕሮጀክቶች አዳዲስ የቱሪስት መዳረሻዎችን በመገንባት የቱሪዝም ዲፕሎማሲን እና ገቢን ለማሳደግ ተሰርቷል ።
በአራተኛነት ማሻሻያው ለማዕድን እና የተፈጥሮ ሀብት ቀን አውጥቷል፡፡
የወርቅ፣ የሌሎች ማዕድናት እና የነዳጅ ፍለጋ ሥራዎችን ሥርዓት ማስያዝ፣ ሕገ-ወጥ ዝውውርን መቆጣጠር እና የውጭ ምንዛሪ ገቢን ለማሳደግ ከፍተኛ ሥራ ተሰርቷል።
የመረጃና ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ላይ የተሠራው ሥራ ደግሞ አምስተኛው ምሰሶ ነው፡፡
የቴሌኮም ዘርፉን ለውድድር ክፍት በማድረግ ሳፋሪኮም ገበያውን እንዲቀላቀል አድርጓል፡፡
በማሻሻያው በዚህ ዘርፍ የዲጂታል ኢኮኖሚን በማፋጠን እና የቴሌኮም መሠረተ ልማትን በማስፋፋት ትልቅ ሥራ ተሠርቷል፡፡
የሀገር በቀል ሪፎርሙ ሁለተኛ ምዕራፍ ከመጀመሪያው እጅግ ደፋር እና ስር ነቀል የሆኑ የማክሮ-ኢኮኖሚ ማሻሻያ እና የገበያ መርህ እርምጃዎችን አካቷል።
ከእነዚህም መካከል የውጭ ምንዛሪ ተመን በገበያ ኃይሎች በአቅርቦትና ፍላጎት እንዲወሰን ማድረግ አንዱና ዋነኛው ነው።
ይህ እርምጃ የጥቁር ገበያውን ክፍተት በማጥበብ የውጭ ምንዛሪን ወደ ሕጋዊ ባንኮች እንዲገባ እና የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት እንዲሁም የሐዋላ ፍሰት በከፍተኛ ደረጃ እንዲያድግ አድርጓል፡፡
ማሻሻያው ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት እንደ ዓለም ባንክ እና አይ ኤም ኤፍ ያሉት ለኢትዮጵያ ያላቸው አመኔታ እና የገንዘብ ድጋፍ ከፍ እንዲል አድርጎታል።
በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው ሀገሪቱ ከተረጂነት እና ከዕዳ ጫና ወጥታ ራሷን ችላ እንድትቆም የሚያደርግ ስልታዊ መሣሪያ ሆኖ እያገለገለ ነው።
ሪፎርሙ የሀገር ውስጥ አቅምን በማንቀሳቀስ፣ የግሉን ዘርፍ በማበረታታት እና የኢኮኖሚ መዋቅሩን በቴክኖሎጂ በመደገፍ የረጅም ጊዜ ብልጽግናን ለማረጋገጥ እየሠራ ይገኛል።
ወቅታዊ፣ ዓለም አቀፋዊና ነባራዊ ተግዳሮቶች ቢኖሩም፣ የተመዘገቡት ስኬቶች የሪፎርሙን ትክክለኛነት እና የኢትዮጵያን ብሩህ ተስፋ የሚያሳዩ ናቸው።