Fana: At a Speed of Life!

በአማራ ክልል 84 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር ገቢ ተሰበሰበ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 25፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአማራ ክልል በተያዘው በጀት ዓመት እስካሁን 84 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር ገቢ ተሰብስቧል አለ የክልሉ ገቢዎች ቢሮ ፡፡
የቢሮው የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ታዘባቸው ጣሴ እንዳሉት ፥ በክልሉ ፍትሃዊ የግብር ሥርዓትን ለማስፈንና የገቢ አቅምን በመለየት አሟጦ ለመጠቀም ቴክኖሎጂ መር የግብር አሰባሰብ ሥርዓት ተዘርግቷል፡፡
በዚህ መሰረትም በክልሉ ከተለያዩ ዘርፎች የሚሰበሰበውን ገቢ ለማሳደግ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት መሰራቱን አመልክተዋል፡፡
በተያዘው በጀት ዓመት እስካሁን 84 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር ገቢ በመሰብሰብ የእቅዱን 83 ነጥብ 9 በመቶ ማሳካት መቻሉን ለፋና ዲጂታል ተናግረዋል፡፡
ከተሰበሰበው ገቢ ውስጥ 74 ነጥብ 3 ቢሊየን ብሩ ከመደበኛ ገቢ የተገኘ ሲሆን÷ 9 ነጥብ 9 ቢሊየን ብሩ ደግሞ ከከተማ አገልግሎት መሆኑን ጠቅሰዋል።
በበጀት ዓመቱ የገቢ አሰባሰቡን ዘመናዊ ለማድረግ በተደረገው ጥረት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የተሻለ ውጤት መመዝገቡን አስረድተዋል፡፡
የግብር አሰባሰቡን ውጤታማነት ይበልጥ ለማሳደግ ሕገ ወጥ ነጋዴዎች ላይ የሚወሰደው ርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው የተናገሩት፡፡
በትዕግስት ግዛቸው
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.