Fana: At a Speed of Life!

የኢኮኖሚ አስተዋጽኦው እያደገ የመጣው የአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ …

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 26፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአምራች ኢንዱስትሪው በቴክኖሎጂ ሽግግር፣ በስራ ዕድል ፈጠራ እና ተኪ ምርት ዘርፎች ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እድገት ከፍተኛ አስተዋፅ እያበረከተ ይገኛል፡፡

ዘርፉ ከግብርና፣ ማዕድን፣ ቱሪዝም እና ዲጂታል ኢኮኖሚ ጋር በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው አንዱ ምሰሶ ተደርጎ መለየቱና ባለፉት ዓመታት የተሰጠው ትኩረት የላቀ ስኬት እንዲያስመዘግብ አስችሎታል።

መንግሥት ለዘርፉ በሰጠው ትኩረት በዘንድሮው ዓመት በተደረጉ አበረታች ማሻሻያዎች የማምረት አቅም አጠቃቀምን ከ46 በመቶ ወደ 61 ነጥብ 8 በመቶ ማሳደግ ተችሏል፡፡

እንደ ግብዓት፣ ፋይናንስ እና የኃይል አቅርቦት ያሉ ተግዳሮቶችን ለመፍታት በተደረገው ጥረትም በዘርፉ የሚፈለገውን ውጤት ለማምጣት መንገድ ጠርጓል።

በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በሥራ ላይ የነበሩ ፋብሪካዎች የማምረት አቅማቸውን እንዲያሳድጉ ከማድረግ ባሻገር ቀደም ሲል በተለያዩ ምክንያቶች ተዘግተው የነበሩ 917 አምራች ኢንዱስትሪዎች ወደ ምርት ሂደት እንዲመለሱ ተደርጓል።

የሀገር ውስጥ የምርት አቅም ዕድገትና የቴክኖሎጂ ሽግግር፣ በዘርፉ የተደረገውን ድጋፍ የሀገር ውስጥ ምርቶች በብዛትና በጥራት እንዲያድጉ ያስቻለ ሲሆን በአሁኑ ወቅት የኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም 66 ነጥብ 3 በመቶ ደርሷል፡፡

በተጨማሪም የማምረት አቅምን ለማሳደግ በሀገር አቀፍ ደረጃ ስራ ላይ ባሉ ከ26 በላይ የግል እና የመንግሥት ኢንዱስትሪ ፓርኮች እና የኢኮኖሚ ዞኖች ለሀገር ውስጥ እና ለውጭ ገበያ የሚውሉ ምርቶችን ከማምረት በተጨማሪ ከፍተኛ የስራ ዕድልን ፈጥሯል፡፡

አሁን ላይ በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ብቻ ከ350 ሺህ በላይ ዜጎች የስራ ዕድል ተጠቃሚ መሆን የቻሉ ሲሆን፤ ለተኪ ምርት በተሰጠው ትኩረት በቢሊየን በሚቆጠር ዶላር ከውጭ ይገቡ የነበሩ ምርቶችን በሀገር ውስጥ መተካት ተችሏል፡፡

የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ እንዲጨምርና ምቹ የኢንቨስትመንት ከባቢ እንዲፈጠር የተደረገው ጥረት የሀገር ውስጥና የውጭ አልሚዎች ተሳትፎ እንዲጨምር አድርጓል።

በተለይም ለዘርፉ ምቹ መደላድል ለመፍጠር የተደረጉ የፋይናንስ እና የሕግ ማዕቀፍ ማሻሻያዎች በአምራች ኢንዱትሪ ዘርፉ ምቹ የኢንቨስትመንት ስነ ምህዳር ፈጥሯል።

በአጠቃላይ የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ እንደ አንቀሳቃሽ ሞተር ሆኖ እያገለገለ ሲሆን፤ በቴክኖሎጂ ሽግግር፣ በስራ ዕድል ፈጠራ እና ተኪ ምርት ዘርፎች ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከተ ይገኛል፡፡

በሚኪያስ አየለ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.