Fana: At a Speed of Life!

በመሶብ የአንድ ማዕክል አገልግሎት ከ3 ሺህ በላይ አገልግሎቶች እየተሰጡ ነው

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 26፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በፌዴራል እና በክልል ስራ በጀመሩ 37 መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎቶች ከ3 ሺህ በላይ አገልግሎቶች ተለይተው ለዜጎች እየተሰጡ ነው አሉ የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽነር መኩሪያ ኃይሌ (ዶ/ር)፡፡

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሃብት ልማት፣ ስራ ስምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽንን የ2018 በጀት ዓመት እቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ገምግሟል፡፡

በዚህ ወቅት መኩሪያ ኃይሌ (ዶ/ር)÷ ተቋማቸው በበጀት ዓመቱ የመንግሥትን መዋቅር ለማዘመንና ብቃት ያለው የሰው ኃይል ለመገንባት በርካታ የሪፎርም ሥራዎች ማከናወኑን አንስተዋል፡፡

በቴክኖሎጂ የታገዘ አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ በፌዴራልና በክልሎች መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎቶችን ለማስፋፋት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም ስራ በጀመሩ 37 መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ከ3 ሺህ 300 በላይ አገልግሎቶች ተለይተው ለዜጎች እየቀረቡ እንደሆነ አመልክተዋል።

በተጨማሪም በበጀት ዓመቱ ሲቪል ሰርቪስ በሳይንሳዊ መንገድ እንዲመራ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንዲሆን ለማድረግ የሙያ እና የሥራ ኢንዱስትሪ ምድብ ሰነድ ተዘጋጅቶ ወደ ትግበራ መገባቱን ገልፀዋል፡፡

ይህም የተቋሙን መዋቅር ዘመናዊ ለማድረግ የጎላ ሚና ይኖረዋል ነው ያሉት፡፡

ኮሚሽኑ ያጋጠሙትን የሶፍትዌር ትግበራና የስታንዳርድ ማፅደቅ ተግዳሮቶች በመፍታት የሪፎርም ስራዎቹን አጠናክሮ እንደሚቀጥል መግለፃቸውን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መረጃ ያመላክታል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር) በሰጡት አስተያየት፤ ዜጎች ባሉበት ሆነው ጊዜ፣ ጉልበትና ሀብት ሳያባክኑ የሚገባቸውን አገልግሎት እንዲያገኙ ለማስቻል የተጀመሩ ስራዎች ተስፋ ሰጪ በመሆናቸው ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ብለዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.