Fana: At a Speed of Life!

በኦሮሚያ ክልል በእንስሳትና ዓሣ ሀብት ልማት ከፍተኛ ስኬት እየተመዘገበ ነው

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 26፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በኦሮሚያ ክልል እየተተገበረ የሚገኘው የእንስሳትና ዓሣ ሀብት ልማት ፕሮጀክት አምራቾችን በዘመናዊ አደረጃጀት በመደገፍ ረገድ ከፍተኛ ስኬት ማስመዝገብ ተችሏል አለ የክልሉ ግብርና ቢሮ።

የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ቶሌራ ደበላ እንዳሉት÷ ፕሮጀክቱ በአርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ ዘንድ የአመጋገብ ሥርዓትን ከማሻሻል ባሻገር በቤተሰብ ደረጃ የገቢ ምንጭን በከፍተኛ ሁኔታ ለማሳደግ አስችሏል።

ይህም መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ እየተገበረው የሚገኘውን የሌማት ትሩፋት ኢኒሼቲቭ ስኬታማ እንዲሆን የጎላ አስተዋጽዖ ማድረጉን አብራርተዋል።

የፕሮጀክቱን አዎንታዊ ተሞክሮዎች ወደ ሌሎች አካባቢዎች ለማስፋፋት እየተሠራ መሆኑን ገልጸው፤ በተለይም የአርሶ አደር የመስክ ትምህርት ቤት አደረጃጀት በመደበኛው የእንስሳት ልማት ኤክስቴንሽን ሥርዓት ውስጥ በማካተት በሁሉም አካባቢዎች ለማስፋፋት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

በፕሮጀክቱ የተገኙ ስኬታማና አርአያነት ያላቸው ተሞክሮዎችን አጠናክሮ በማስቀጠል የዘርፉን ምርታማነት ለማሳደግ ሁሉም ባለድርሻ አካላትና አጋሮች የበኩላቸውን ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

የኦሮሚያ ክልል የእንስሳትና ዓሣ ሀብት ልማት ፕሮጀክት አስተባባሪ ደረጄ ጉደታ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ በክልል ደረጃ ከ4 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች፣ ወጣቶች እና ሴቶችን በማደራጀትና ተገቢውን ድጋፍ በማድረግ ወደ ሥራ ማስገባት መቻሉን አንስተዋል።

ከተደራጁት ወገኖች መካከል ውጤታማና ትርፋማ የሆኑ 2 ሺህ 118 የሚሆኑ አምራቾችን ወደ ማሕበራት ማሳደግ መቻሉን ገልጸዋል።

ማህበራቱ ወደ ሥራ ከመግባታቸው አስቀድሞ ለሥራው የሚያስፈልጋቸውን መሠረተ ልማት፣ መሣሪያዎች፣ ግብዓቶች እና ተግባራዊ ዕውቀት እንዲያገኙ መደረጉንም አክለው አስረድተዋል።

ፕሮጀክቱ ያስመዘገበው ውጤት ከተጠበቀው በላይ መሆኑን ገልጸው፤ ዘርፉ ተገቢው ትኩረትና ድጋፍ ከተሰጠው በሀገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት ውስጥ የላቀ ሚና መጫወት እንደሚችል በተግባር ያሳየ ነው ብለዋል።

በዮናስ ጌትነት

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.