ገበታ ለትውልድ፣ የኢትዮጵያን ጸጋዎች ለቀጣዩ ትውልድ ሀብት የማድረግ ጉዞ
የገበታ ለትውልድ ፕሮጀክት የኢትዮጵያን የተፈጥሮ ውበት ወደ ላቀ ኢኮኖሚያዊ እሴት የቀየረ ስልታዊ ልማት ነው፡፡
ይህ ፕሮጀክት የተፈጥሮ እና የታሪክ ቅርሶችን በአግባቡ ጠብቆ በማልማት፣ የዛሬውን ትውልድ ተጠቃሚነት ከማረጋገጥም በላይ ለቀጣዩ ትውልድ የሚተርፍ ታላቅ ሀገራዊ ሀብት ጥሎ የሚያልፍ ዘላቂ መርሃ-ግብር ሆኗል፡፡
ገበታ ለትውልድ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) አነሳሽነት ይፋ የሆነ እና የኢትዮጵያን እምቅ የቱሪዝም እና የተፈጥሮ ሀብት ወደ ላቀ የኢኮኖሚ አቅም ለመቀየር ያለመ ግዙፍ ብሔራዊ ፕሮጀክት ነው።
ዕቅዱ የኢኮኖሚ ብዝሃነት፣ የሥራ ዕድል ፈጠራ፣ የአካባቢ ጥበቃ እና ልማትን የማረጋገጥ ዓላማ አለው፡፡
ይህ መርሃ-ግብር ቀደም ሲል ስኬታማ በሆኑት የገበታ ለሸገር እና ገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶች ተሞክሮ ላይ በመመስረት፣ አድማሱን ወደ ተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በማስፋት አዳዲስ ታላላቅ የቱሪስት መዳረሻዎችን ለማልማት ይተጋል፡፡
ፕሮጀክቱ በዋናነት ፋይናንስ የተደረገው ከመንግስት በጀት ውጭ በሆነ መንገድ ሲሆን፣ የመደመር ትውልድ መጽሐፍ ሽያጭ ገቢ፣ ከሀገር ውስጥና ከውጭ ባለሀብቶች፣ ከዲያስፖራው ማህበረሰብ እንዲሁም ከተለያዩ ተቋማት በተሰበሰበ ድጋፍ ነው።
ገበታ ለትውልድ የሀገሪቱን የገቢ ምንጭ ከግብርና ወደ አገልግሎት እና ወደ ቱሪዝም ዘርፍ ለማሸጋገር ያለመ ሲሆን፣ ልማቱ በግንባታ፣ በሆቴልና በእንግዳ ተቀባይነት ዘርፎች ለበርካታ ወጣቶችና የአካባቢው ነዋሪዎች ሰፊ የሥራ ዕድል እየፈጠረ ይገኛል፡፡
በዕቅድ ትግበራው የተፈጥሮ ደኖችን፣ ወንዞችን እና የሐይቆችን ነባራዊ ውበት ሳይበክል የቱሪስት መሠረተ ልማቶችን ለማሟላት እየተሰራ ነው።
ይህንን ፕሮጀክት ተከትሎ የተዘረጉ መንገዶች፣ የንጹህ ውሃ አቅርቦት፣ የኤሌክትሪክ ኃይል መስመሮች እና የቴሌኮም መሠረተ ልማቶች ቀደም ሲል አገልግሎት ያጡ የነበሩ የገጠር መንደሮችን ወደ መካከለኛ ከተማነት እንዲቀየሩ እና የአካባቢውን ማህበረሰብ የኑሮ ደረጃ እንዲሻሻል እያደረጉት ይገኛሉ፡፡
ከዚህ ባለፈም የቱሪዝም እና የእንግዳ ተቀባይነት ዘርፍን በማነቃቃት የሀገሪቱን የገቢ ምንጭ እያሰፉ ነው፡፡
ዘመናዊ መዳረሻዎችን በዓለም አቀፍ ደረጃ በማስተዋወቅ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ፍሰት ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገባ የሚያስችል ዘላቂ የኢኮኖሚ መሠረትም ይጥላሉ፡፡
የገበታ ለትውልድ መዳረሻዎች ሀሮ ደንዲ ሎጅ፣ ሸበሌ ሪዞርት፣ ኒዒን ሌ ፓልም ሎጅ፣ ሎጎ ሐይቅ ሪዞርት፣ የአርባ ምንጭ ኮንፈረንስ ሪዞርት፣ የጅማ ቦዬ ሳይት፣ የገርዓልታ እና በታላቁ የሕዳሴ ግድብ ዙሪያ የተፈጠረውን ሰው ሰራሽ ሐይቅ እና ጥቅጥቅ ያሉ ደኖችን ለውኃ ላይ ስፖርት እና ለመዝናኛ አገልግሎት ማዋልን ያካተቱ ናቸው፡፡
ገበታ ለትውልድ የኢትዮጵያን ያልተነኩ የተፈጥሮ መስህቦች በአግባቡ በማልማት ሀገሪቱ በቱሪዝም ዘርፍ ያላትን ተወዳዳሪነት ከፍ እያደረጉት ይገኛሉ።
እነዚህ መዳረሻዎች የዛሬውን ትውልድ የኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ከማረጋገጣቸውም በላይ፣ የተፈጥሮ ቅርስን ጠብቆ ለቀጣዩ ትውልድ የማስተላለፍ ትልቅ ብሔራዊ ራዕይ መገለጫዎች ናቸው።
በአጠቃላይ የገበታ ለሸገር፣ ገበታ ለሀገር እና ገበታ ለትውልድ ፕሮጀክቶች የኢትዮጵያን ትክክለኛ መልክ እየገለጡ ለዓለም እያሳዩ ይገኛሉ፡፡
ሀገሪቷ በዓለም አቀፍ መድረክ በአረንጓዴ ልማት፣ በተፈጥሮ ውበት እና በዘመናዊ መሠረተ ልማት እንድትታወቅ በማድረግ ረገድ አዎንታዊ ገጽታን እየገነቡ ነው።
ከዚህ በተጨማሪም፣ የሀገር ውስጥ ቱሪዝምን በማበረታታት ዜጎች በሀገራቸው ውስጥ ተዘዋውረው እንዲዝናኑ፣ ባህልና ማንነታቸውን ይበልጥ እንዲያውቁ እና ማህበረሰባዊ ትስስር እንዲጠናከር እያደረጉ ነው፡፡