Fana: At a Speed of Life!

የሀብት ማከፋፈያ ቀመሮች በአግባቡ መተግበራቸውን በቅርበት መከታተል ተችሏል – አቶ ሽመልስ አብዲሳ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 28፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በበጀት ዓመቱ የሀብት ማከፋፈያ ቀመሮች በአግባቡ መተግበራቸውን በቅርበት መከታተል ተችሏል አሉ የፌዴሬሽን ምክር ቤት የድጎማ በጀትና የጋራ ገቢዎች ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ሽመልስ አብዲሳ።

አቶ ሽመልስ አብዲሳ እንዳሉት፤ በ2018 በጀት ዓመት በክልሎች መካከል የተመጣጠነ ልማትንና የዜጎችን ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በርካታ ውጤታማ ሥራዎችን አከናውኗል።

የድጎማ በጀትና የጋራ ገቢዎች ክፍፍል ሥርዓት በጥናትና በተደራጀ ዕቅድ እንዲመራ ከማድረግ ባሻገር ወደ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የሚተላለፉ ሀብቶች ግልጽና ፍትሐዊ በሆነ መንገድ እንዲከፋፈሉ ክትትልና ድጋፍ መደረጉን ተናግረዋል።

በበጀት ዓመቱ የሀብት ማከፋፈያ ቀመሮች በአግባቡ መተግበራቸውን በቅርበት መከታተል መቻሉን ገልጸው÷ ይህም የሚተላለፉ ሀብቶች ላይ ግልጽነትን ለማሳደግና የበይነ መንግሥታት የፊስካል ሽግግር ሥርዓትን ለማጠናከር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን አብራርተዋል።

በተጨማሪም የፌዴራል መሠረተ ልማት ስርጭት ፍትሐዊነትን ማስፈን እንዲሁም ልዩ ዓላማ ያላቸው ድጎማዎች በግልጽነትና በተጠያቂነት መርህ ለክልሎች መከፋፈላቸውን ማረጋገጥ የኮሚቴው ዋና ዋና ስትራቴጂካዊ ተግባራት እንደነበሩ አመልክተዋል።

የኢኮኖሚና የማሕበራዊ ዕድገትን ማፋጠንና በክልሎች መካከል ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን እውን ማድረግ የረጅም ጊዜ ጥረት እንደሚጠይቅ ገልጸው ማነቆዎችን በመለየትና መረጃዎችን በወቅቱ በማሰባሰብ ዘላቂ መፍትሔዎችን ለማምጣት ይሰራል ማለታቸውን የፌዴሬሽን ምክር ቤት መረጃ አመልክቷል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.