የሕገ ወጡ ህወሓት ቡድን አስገዳጅ አፈሳ የቡድኑ ተቀባይነት ማክተሙን ያሳያል – የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 1፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የሕገ ወጡ ህወሓት ቡድን የአስገዳጅ አፈሳ እና የእገታ ድርጊቶች የቡድኑ ተቀባይነት ሙሉ በሙሉ ማክተሙን ያመላከተ ነው አሉ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች።
ባለሙያዎቹ በትግራይ ክልል የተለያዩ የግል ጥቅሞችንና ፍላጎቶችን ለማሳካት ሲባል በሕዝቡ ላይ የሚፈጸመው አስገዳጅ የአፈሳ እና የእገታ ድርጊቶች በከፍተኛ ሁኔታ መቀጠሉን ተናግረዋል፡፡
ድርጊቱ በክልሉ ሕዝብ ዘንድ ከፍተኛ ተቃውሞ እንደገጠመውም ነው ያመላከቱት፡፡
የአውራምባ ታይምስ ጋዜጠኛ ዳዊት ከበደ እንዳለው÷ ድርጊቱን እየፈጸሙ ያሉ አካላት ከወርቅ እና ማዕድን ንግድ ጋር የተያያዙ በርካታ የግል ጥቅሞች አሏቸው።
እነዚህን ጥቅሞች ለማስጠበቅ ሲባልም ተፈናቃዮችን ለማስመለስ የሚሉ ምክንያቶችን እንደ ሽፋን ወይም ማስተባበያ እየተጠቀሙ እንደሆነና አሁን የሚያደርጉት እንቅስቃሴ በማኅበረሰቡ ዘንድ ውድቅ መደረጉን አመልክቷል።
በዚህም ምክንያት ወጣቶችን በኃይል ወደ ማሰልጠኛዎች ማስገባትና አስገዳጅ አፈሳዎችን ማካሄድ መጀመራቸውን ጠቁሟል።
አሁን ላይ ድርጊቱ ተባብሶ የሕዝብ ማመላለሻ አውቶቡሶችን ጭምር በማስቆም ወጣቶችን የማስቀረት ተግባር እያከናወኑ መሆኑን ጠቅሶ÷ ይህም እጅግ የሚያሳዝን ሁኔታ መሆኑን አብራርቷል።
ጋዜጠኛ ሄርሞን ፍቃዱ በበኩሏ÷ የህወሓት ጽንፈኛ አመራሮችና የጥፋት ኃይሎች እየፈጸሙ ያሉትን ድርጊት በጽኑ አውግዛለች፡፡
በአሁኑ ዘመን የፕሮፓጋንዳ ፍላጎታቸውን ለማሳካት ሲባል ሰዎችን በግድ ማገትና ማፈስ የማይጠበቅና እጅግ የወረደ ድርጊት መሆኑን አስገንዝባለች።
ይህ ቡድን ከቀደመው ስህተቱ መማር አልቻለም ያሉት ደግሞ የትንሳኤ ሰብዓ እንደርታ ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አብረሃም ፅጌ ናቸው።
ሕዝቡ አሁን ላይ ያለፈው ይበቃናል ፤ ከዚህ በኋላ ዳግም ስህተት ውስጥ አንገባም ማለቱ የቡድኑ ተቀባይነት ሙሉ በሙሉ ማክተሙን ያሳየ ነው ሲሉ ለኢዜአ ገልዋል፡፡