Fana: At a Speed of Life!

በመምከራቸው ሀገር የገነቡ ሀገራት…

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 2፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በዓለም ታሪክ ውስጥ በጦርነት፣ በድህነትና በከባድ ማሕበራዊ ቀውስ ውስጥ አልፈው ዛሬ ላይ የብልጽግና ማማ ላይ የደረሱ ሀገራት አሉ።

የእነዚህ ሀገራት የስኬት ምስጢር የተፈጥሮ ሀብት ሳይሆን፤ በአስቸጋሪ ወቅት ተቀምጠው የመከሩበት እና የጋራ ብሔራዊ መግባባት የፈጠሩበት የምክክር ጥበብ ነው።

ለአብነትም አፍሪካዊቷ ሀገር ደቡብ አፍሪካ በምክክር ሀገር እንዴት መቀጠል እንደሚችል ማሳያ ናት።

በደቡብ አፍሪካ አፓርታይድ ሥርዓት ካበቃ በኋላ ሀገሪቱ ወደ ከፍተኛ የእርስ በርስ ጦርነት ልታመራ ትችል የነበረ ቢሆንም የፖለቲካ እና የማሕበራዊ መሪዎች ተቀምጠው በመምከራቸው ሁሉንም ያካተተች ደቡብ አፍሪካን ገንብተዋል፡፡

ሌላኛዋ ሀገር ሩዋንዳ በሀገሪቱ ከደረሰው የዘር ማጥፋት በኋላ ሕዝቡ ባሕላዊ የምክክርና የእርቅ ሥርዓትን በመጠቀም ቂምን በይቅርታ መተካት ችለዋል፡፡

ከኮሪያ ጦርነት በኋላ ከፍተኛ የድህነት ቀውስ ውስጥ የገባችው ደቡብ ኮሪያ በወቅቱ የሀገሪቱ መንግሥት፣ ሰራተኛው እና ባለሀብቱ በጋራ በመምከራቸው ሀገራዊ ጥቅምን ያስቀደመ ስምምነት አድርገዋል፡፡

ለዘመናት በነበረው የሃይማኖትና የፖለቲካ ግጭት ትታመስ የነበረችው አየርላንድ በጠረጴዛ ዙሪያ በተደረገ ሰላማዊ ምክክር ዛሬ ካሉ የበለጸጉ የአውሮፓ ሀገራት ተርታ ተሰልፋለች።

የደቡብ አፍሪካ፣ የሩዋንዳ እና የሌሎች ሀገራት ተሞክሮ የሚያሳየው መምከር የውድቀት ማቆሚያ፤ የብልጽግና መጀመሪያ መሆኑን ነው።

ኢትዮጵያም ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ክፍተቶቿን ለመፍታት በታሪኳ ትልቅ የተባለለትን የሀገራዊ ምክክር ሂደት እያከናወነች ትገኛለች።

ምክክሩ ለዘመናት የዘለቁ የትርክት ልዩነቶችን፣ የታሪክ ቅሬታዎችን እና የማንነት ጥያቄዎችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ያለመ ነው።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች አጀንዳዎችን በማሰባሰብ ህዝቡ በነጻነት እንዲወያይ እና በጋራ እጣ ፈንታው ላይ እንዲወስን እያደረገ ይገኛል።

ኮሚሽኑ ሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ሁሉንም ያሳተፈ ታሪካዊ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ የሚያካሂድ ይሆናል፡፡

በጉባኤው ለመታደም ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች የተወጣጡ የህብረተሰብ ተወካዮች እና ተሳታፊዎች ወደ አዲስ አበባ በመግባት ላይ ናቸው።

የምክክር ጉባኤው ለዘመናት የቆዩ ሀገራዊ ልዩነቶችን በውይይት ፈትቶ ለዘላቂ ሰላምና ጠንካራ ሃገር ግንባታ ጽኑ መሠረት ይጥላል ተብሎ ይጠበቃል።

በሶስና አለማየሁ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.