Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ የምስራቅ አፍሪካ የኃይል ትስስር የሚኒስትሮች ም/ቤት ሰብሳቢ ሆነች

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 2፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ የምስራቅ አፍሪካ የኃይል ትስስር የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሰብሳቢነትን ከግብጽ ተረክባለች።

በትናንትናው ዕለት በአዲስ አበባ የተጀመረው 37ኛው የምስራቅ አፍሪካ ኃይል ትስስር ስቲሪንግ ኮሚቴ ልዩ ስብሰባ ዛሬም ቀጥሎ ተካሂዷል፡፡

በመድረኩ የተገኙት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ሃብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) ÷ በጥምረቱ የሕግ የበላይነት እና የድርጅቱ መመስረቻ ስምምነት ያለ ልዩነት መከበር እንዳለበት አጽንኦት ሰጥተዋል።

ከዚህ ቀደም በሰብሳቢነት ሽግግር ላይ ልዩነት ተፈጥሮ እንደነበር ጠቁመው÷ በሕጉ በተቀመጠው ቅደም ተከተል መሰረት ኢትዮጵያ መሪነቱን መረከቧ የሕግ የበላይነት ማረጋገጫ መሆኑን ገልጸዋል።

ከአንድ በላይ ዋና መሥሪያ ቤቶችን ከመሰየምና የገበያ ኦፕሬተሩን አስተናጋጅ ሀገር ከመምረጥ ጋር ተያይዞ የተፈጠሩ ሕጋዊ አለመግባባቶችንና መሰናክሎችን ለመፍታት የሥራ አመራር ኮሚቴው ሙሉ በሙሉ የተስማማበትን የውሳኔ ምክረ ሀሳብ ማቅረቡ ተመላክቷል።

የምክር ቤቱ አባላት ምክረ ሀሳቡን በማጽደቅ የቀጣናውን የኃይል ገበያና አንድነት እንዲያጠናክሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ኢትዮጵያ የምስራቅ አፍሪካ ኃይል ትስስር አባል ሀገራት የኤሌክትሪክ ገበያ ወደ ሥራ በፍጥነት እንዲገባ መጠየቋም የሚታወስ ነው፡፡

በዘቢብ ተክላይ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.