Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ ቀጣናዊ ሰላም እንዲሰፍን በቁርጠኝን እየሰራች ነው – አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 3፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ኢትዮጵያ ለቀጣናዊ ዘላቂ ሰላም መስፈን በቁርጠኝን እየሰራች ነው አሉ።

ዋና ትኩረቱን በፓርላማ አባላት፣ በመረጃ ባለሙያዎችና በመንግሥት ባለስልጣናት መካከል በዓለም አቀፍ የደህንነት ስጋቶች ዙሪያ ትብብር ለማጎልበት ያደረገ ዓለም አቀፉ የፓርላማ የመረጃና ደህንነት ፎረም መካሄድ ጀምሯል።

አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ በፎረሙ ላይ እንዳሉት፤ ረጅም ዘመን ያስቆጠረ የዴሞክራሲ ልምድ ያላት ኢትዮጵያ ደህንነት እና ሰላምን ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት እየሰራች ትገኛለች።

ኢትዮጵያ ወሳኝ ሀገራዊ ምርጫ ባደረገችበት ማግስት እየተካሄደ ያለው ፎረሙ የዴሞክራሲያዊ አስተዳደርን ለማረጋገጥ እንደሚያግዝ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ላይ ሰላማዊና አካታች ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ማድረጓን አስታውሰው፤ ኢትዮጵያ በምርጫው ትልቅ አቅም በመገንባት ለዴሞክራሲ መዳበር ያላትን ቁርጠኝነት አረጋግጣለች ብለዋል።

የዓለም የደህንነት ጉዳይ ተለዋዋጭና አስተማማኝ ባልሆነበት በአሁኑ ወቅት መተባበር እንደሚያስፈልግ ጠቅሰው፤ ይህ ፎረም በሀገራት መካከል ያለውን ትብብር ለማጠናከር ዝግጁነት እንዳለ የሚያሳይ መሆኑን አስረድተዋል።

የአፍሪካ ቀንድ ቀጣና አክራሪነትን፣ ግጭቶችን፣ የአየር ንብረት ለውጥንና የሳይበር ጥቃቶችን በስፋት እየተጋፈጠ እንደሚገኝ አንስተዋል።

ህገወጥ የሰዎች ዝውውርን፣ ስደተኝነትንና የሳይበር ጥቃትን በጋራ መከላከል እንደሚገባ ገልጸው፤ ችግሩን ለመፍታት አፍሪካ “አፍሪካዊ መፍትሄዎች ለአፍሪካ ችግሮች” የሚለውን መርህ በመከተል ውጤታማ ስራዎችን እያከናወነች እንደሚገኝ አጽንኦት ሰጥተዋል።

ኢትዮጵያ ቀጣናዊ ሰላም እንዲሰፍን የሽብር ቡድኖችን በመዋጋት ረገድ በቁርጠኝነት እየሰራች ትገኛለች ያሉት አፈ ጉባኤው፤ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከልና ስደትን ከምንጩ ለማስቀረት ሰፊ የሥራ ዕድል ለመፍጠር ትኩረት መሰጠቱን ተናግረዋል።

በሕብረተሰብ ጤና አጠባበቅ ላይ በተሰራው ሥራ አጋጥሞ የነበረውን ወረርሽኝ መቆጣጠር እንደተቻለ አንስተው፤ በሰው ሰራሽ አስተውህሎት ቴክኖሎጂዎች ላይ ተቋማዊ አቅምን የማሳደግ ስራዎች በስኬት እየተከናወኑ መሆኑን አስገንዝበዋል።

በዓለምሰገድ አሳዬ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.