ኢትዮጵያ የሁሉም ኢትዮጵያውያን በመሆኗ ያለያዩንን ጉዳዮች በምክክር እንፈታለን – መስፍን አርአያ (ፕ/ር)
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 5፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ የሁሉም ኢትዮጵያውያን በመሆኗ ያለያዩንን ጉዳዮች በምክክር እንፈታለን አሉ የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርአያ (ፕ/ር)፡፡
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን “ኢትዮጵያ እየመከረች ነው” በሚል መሪ ሀሳብ በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ ያዘጋጀው የ5 ኪሎ ሜትር ሩጫ የጎዳና ላይ ሩጫ ተካሂዷል።
በሩጫ ውድድሩ ላይ አካል ጉዳተኞችን ጨምሮ በሁሉም የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍል የመጡ ከ20 ሺህ በላይ ዜጎች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡
ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርአያ (ፕ/ር) ውድድሩን ባስጀመሩበት ወቅት ባስተላለፉት የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት፥ ኢትዮጵያ የሁሉም ኢትዮጵያውያን መሆኗን አውስተዋል፡፡
ኢትዮጵያ የሁሉም ኢትዮጵያውያን በመሆኗ እስከዛሬ ያለያዩን፣ ያቀያየሙን እና ያኮራረፉንን ጉዳዮች በመካከር እንፈታለን ነው ያሉት።
በሩጫ መርሐ ግብሩ ላይ ኢትዮጵያ እየመከረች ነው፣ በምክክር ከስጋት ወደ መግባባት፣ በምክክር ሁሉም አሸናፊ የሚሉና ሌሎች መልዕክቶች ተላልፈዋል፡፡
ኢትዮጵያ ለዘመናት ሲፈጠሩ ለነበሩ ልዩነቶችና አለመግባባቶች በዘላቂነት ለመፍታት ባለፉት አመታት በምክክር ሂደት ውስጥ የምትገኝ ሲሆን፥ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ በመጪው ረቡዕ ሐምሌ 8/2018 ይጀመራል፡፡
በሚልኪያስ አዱኛ