ከመላው ኢትዮጵያዊ ጋር ሆነን እዚህ ደርሰናል – መስፍን አርዓያ (ፕ/ር)
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 8፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርዓያ (ፕ/ር) ከመላው ኢትዮጵያዊ ጋር ሆነን እዚህ ደርሰናል አሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር በዛሬው ዕለት በይፋ መካሄድ ጀምሯል።
መስፍን አርዓያ (ፕ/ር) በመድረኩ ላይ፥ ዛሬ የተሰባሰብነው በታሪክ ምእራፍ ላይ ስፍራን ለሚይዝ ታላቅ ጉዳይ ነው ብለዋል።
ጉባኤው የፖለቲካና ማሕበራዊ ጉዞ የሚያጸና፣ ለቀጣዩ ትውልድ ጠንካራ ሀገር ለመገንባት የሚያስችል አዲስ የታሪክ ምዕራፍ የሚከፍት ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ የሚያኮሩ ባህሎችና የብዝሃ ውበት ባለቤት ብትሆንም ይህን በታላቅነት ለማስቀጠል እንቅፋት በሆኑ በርካታ የሃሳብ ልዩነቶችና አለመግባባቶች ማለፏ አይካድም ነው ያሉት።
እነዚህ የተከማቹ፣ ለዘመናት የቆዩ የፖለቲካና የስርዓት ጥያቄዎች የዜጎችን ሰላምና የሀገር አንድነትን እየፈተኑ እንደሚገኙ አስረድተዋል።
አመለካከቶቻችን የማንነታችን አካል ናቸው ያሉት ዋና ኮሚሽነሩ፤ እነዚህ ልዩነቶቻችን ችግር የሚሆኑት ግን ልዩነቶቻችንን በምክክር ፋንታ በግጭት፣ በመገለልና በኩርፊያ ወይም በሃይል ለመፍታት ሲሞከር ነው ሲሉም አብራርተዋል።
ለዚህም መፍትሄው ታማኝ፣ አካታች፣ ግልጽና ሳይንሳዊ የሆነ ምክክር ማካሄድ ነው ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል።
ዛሬ ምንጀምረው ጉባኤ እርስ በእርስ እንድንደማመጥ፣ የሌላውን ህመም እንድንረዳ፣ በየጊዜው የሚያመረቅዙ ትርክቶችንና የታሪክ ጠባሳዎችን እንዲሽሩ ለማድረግ በጋራ የወደፊት እጣ ፈንታችን ላይ እንድንስማማ ትልቅ እድል የሚሰጥ ሀገራዊ ፈውስ የምናደርግበት ነው ብለዋል።
ኮሚሽኑ በየደረጃው ሰፊ የአጀንዳ ማሰባሰብ ስራዎችን፣ ለህዝቡ ግንዛቤ የመፍጠር ስራ መስራቱንና በአጠቃላይ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ በርካታ ስራዎችን በመስራት ለዛሬው ታሪካዊ ጉባኤ መድረስ መቻሉን አስገንዝበዋል።
ከጉባኤው የምንጠብቃቸው ውጤቶች የሀገራችንን እጣፈንታ የሚወስኑ ናቸው ብለዋል።
የጋራ መፍትሄ በማስቀመጥ ዘላቂ ሰላም እና መረጋጋት ማስፈንና የውይይትና የምክክር ባህልን በኢትዮጵያ መትከል ይጠበቅብናል ሲሉም ተናግረዋል።
አክለውም ከጠበበ የቡድንና የግል ፍላጎት ወጥተን ለሀገር ሰላምና ለቀጣዩ ትውልድ እጣፈንታ ስንል በቅንነት፣ በሃቀኝነት እንድንመክር ሲሉ አሳስበዋል።
በሶስና አለማየሁ