Fana: At a Speed of Life!

ለቀጣዩ ትውልድ የሚተርፍ መልካም ዘሮች የሚዘሩበት ጉባኤ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 8፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በታሪኳ አዲስ ምዕራፍ ለመክፈትና ለዘመናት የዘለቁ ውስብስብ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ እና የማህበራዊ ትስስር ክፍተቶችን በውይይት ለመፍታት ወሳኝ ወቅት ላይ ትገኛለች።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከመላው የሀገሪቱ ክፍሎችና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን የወከሉ የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎችን በማሰባሰብ የጀመረው ሂደት የሀገራዊ ምክክር ሂደት ዛሬ ላይ ስምንት አጀንዳዎችን ለይቶ የምክክር ጉባኤ ከዛሬ ጀምሮ እያካሄደ ነው።

ይህ ጉዞ ኢትዮጵያ ካለፉት የትኩረት ነጥቦች በመውጣት፣ ወደ ተሻለ ብሔራዊ መግባባትና ዘላቂ ሰላም ለመሸጋገር የምታደርገው የታሪካዊ ጉዞ መገለጫ ነው።

ትልቅ ምዕራፍ ላይ የደረሰው ይህ ጉዞ ከነገ ከዛሬ ሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ የሁሉንም የህብረተሰብ ክፍሎች ተወካዮች በማሳተፍ እየተካሄደ ይገኛል።

በሀገራዊ ምክክር ጉባኤው የሚሳተፉት ከመላው የሀገሪቱ ክፍሎች፣ ከፌዴራል ተቋማት፣ ከፖለቲካ ፓርቲዎች እና ከዳያስፖራው ማኅበረሰብ የተውጣጡ ከ4 ሺህ በላይ ተመካካሪዎች ናቸው።

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ለጉባኤው ተሳታፊዎች በሙሉ ስለ ውይይቱ ሥነ ምግባር፣ ሥርዓት እና የአሰራር ደንብ የቅድመ ምክክር ግንዛቤ ማስጨበጫ ገለጻ አድርጓል፡፡

የዚህ ታሪካዊ ጉባኤ ዋነኛ ግብ አሸናፊና ተሸናፊ የሚገኝበትን የቆየ የፖለቲካ ባህል በመቀየር፤ ሁሉም በጋራ የሚያሸንፍበትን ብሔራዊ መግባባት የመፍጠር ዓላማ አለው።

ተመካካሪዎች በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም፣ ዴሞክራሲ፣ ሰብዓዊ መብቶች እና የሀገር ግንባታ ዙሪያ ጨምሮ የቀረቡትን ዋና ዋና የአጀንዳ ምሰሶዎች በጥንቃቄ በመመርመር የጋራ መፍትሔዎችን ያስቀምጣሉ።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ባስተላለፉት መልዕክት፤ ይህ ታላቅ የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ፣ ኢትዮጵያ በገዛ እጇ አዲስ ታሪክ ለመጻፍ የሚያስችላትን “ብዕርና ብራና” ያገኘችበት ታሪካዊ አጋጣሚ ነው ብለዋል።

‎የኢትዮጵያ የፖለቲካ ጉዞ በኃይለ ቃል ጀምሮ በኃይል እርምጃ የሚደመደምበትን አዙሪት ሰብረን በንግግርና በውይይት የምንተካበት ወቅት ላይ እንገኛለን ሲሉም ገልጸዋል።

የሀገራዊ ምክክር ጉባኤው በቀላሉ የማይደገም እና በኢትዮጵያ ዘመናዊ ታሪክ ውስጥ ግዙፍና ታላቅ ዓላማ ያለው መሆኑንም አስገንዝበዋል።

ፈተናዎቻችንን ወደ መልካም አጋጣሚዎች በመቀየር ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር ባህልን እናጸናለን በማለት ገልጸው፤ ለቀጣዩ ትውልድ የሚተርፍ መልካም ዘሮችን እንዘራለን፤ ከሚያፈራውም ፍሬ ልጆቻችን እንዲጠቀሙ እናደርጋለን ነው ያሉት።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.