Fana: At a Speed of Life!

 የኦሮሚያ ቡሳ ጎኖፋ ለሚከሰቱ አደጋዎች ምላሽ የመስጠት አቅሙን እያጠናከረ መጥቷል

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 10፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ሶስተኛው የኦሮሚያ ቡሳ ጎኖፋ አባላት ማጠቃለያ ጉባኤ በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል፡፡

በመድረኩ የተገኙት የቡሳ ጎኖፋ ኃላፊ መሀመድ ጁንዲ÷ ቡሳ ጎኖፋ በቀበሌ፣ ወረዳ እና ዞን አሰራሩን በማቀናጀት በክልሉ ለሚከሰቱ አደጋዎች የሚሰጠውን ምላሽ እያጠናከረ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡

በተለይም ተፈናቃዮችንና ተጎጂዎችን በማጣራት፣ የሴፍቲኔት ፕሮግራምን እና እርዳታዎችን ተደራሽ በማድረግ ረገድ በርካታ ስራዎችን ማከናወን መቻሉን ጠቁመዋል፡፡

ተረጂዎች ብሔራዊ መታወቂያ እንዲኖራቸው ማድረግ ተችሏል ያሉት ኃላፊው÷ ይህም እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን ሰዎች ለመለየት እና እርዳታዎችን በፍትሐዊነት ለማዳረስ አስችሏል ነው ያሉት፡፡

በዓመቱ 3 ቢሊየን ብር ገቢ ለማግኘት በማቀድ 2 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር መሰብሰብ መቻሉን ጠቁመው፤ በዚህም ቡሳ ጎኖፋ ከእርዳታ አቅራቢነት ባሻገር ወደ ምርታማነት መሸጋገር መቻሉን አመላክተዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ 1 ሚሊየን የቡሳ ጎኖፋ አባላትን ለመጨመር ታቅዶ 2 ነጥብ 1 ሚሊየን አባላትን ማስገባት መቻሉን ገልጸው÷ አሁን ላይ የቡሳ ጎኖፋ የአባላቱ ቁጥር ከ29 ሚሊየን ማለፉን ጠቁመዋል።

በሀገር ውስጥ እና በውጪ የሚኖሩ ዜጎች ችግር ሲፈጠር አፋጣኝ መፍትሔ ለመስጠት የሚያስችል አቅም ለመፍጠር የቡሳ ጎኖፋ አባል በመሆን ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በአቤል ነዋይ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.