Fana: At a Speed of Life!

በአማራ ክልል የሌማት ትሩፋት በፈጠረው መነቃቃት ከ36 ሺህ ቶን በላይ የማር ምርት ተገኘ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 10፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአማራ ክልል በ2018 በጀት ዓመት የሌማት ትሩፋት መርሐ ግብር በፈጠረው መነቃቃት ከ36 ሺህ ቶን በላይ የማር ምርት ተገኝቷል አለ የክልሉ እንስሳትና ዓሣ ሀብት ልማት ቢሮ፡፡

የቢሮው ኃላፊ ጋሻው ሙጨ (ዶ/ር) ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን እንደገለፁት÷ በክልሉ በሌማት ትሩፋት መርሐ ግብር አማካኝነት የወተት ላሞች፣ የንብ፣ የዶሮ እና የዓሣ ሃብት ልማት ላይ ከፍተኛ ውጤት ተመዝግቧል።

በንብ ማነብ በተሰራው ስራ የማር ምርታማነት ማደጉን ገልጸው፤ በበጀት ዓመቱ 33 ሺህ 333 ቶን ማር ለማምረት ታቅዶ ከ36 ሺህ 665 ቶን ማር ማምረት መቻሉን ተናግረዋል።

ከታቀደው በላይ ስኬት ማስመዘገብ የተቻለው በሌማት ትሩፋት መርሐ ግብር አማካኝነት በተፈጠረው መነቃቃት ነው ብለዋል።

የቅድመ ምርት ስራዎች ላይ ከፍተኛ ክትትል መደረጉ እና ዘመናዊና የሽግግር ቀፎ ግብዓት አቅርቦት ተደራሽ ማድረግ መቻሉ ለተገኘው ከፍተኛ የማር ምርት አስተዋፅኦ ማድረጋቸውን ጠቅሰዋል፡፡

ምርታማነትን ከማሳደግ ጎን ለጎን የገበያ ትስስር በመፍጠር የንብ አናቢዎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተሰራ መሆኑንም አመላክተዋል፡፡

በከድር መሀመድ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.