Fana: At a Speed of Life!

ጋዜጣ ሲያነቡ ባገኙት የስራ ማስታወቂያ ወደ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝነት የመጡት ሉዊስ ዴላፎንቴ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 11፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ወቅቱ የስፔን እግር ኳስ ፌዴሬሽን ብሔራዊ ቡድኑን ወደ አሸናፊነት የሚያመጣ ሰው የሚፈልግበት ጊዜ ነበር፡፡

ግን በቂ ገንዘብ ስላልነበረው በክፍያ የማይደራደር እና በሚሰጠው እድል ተስማምቶ የሚሰራ አሰልጣኝ ለአዳጊ ቡድን እንፈልጋለን የሚል ማስታወቂያ በጋዜጣ አወጣ።

ወቅቱ ሉዊስ ዴላፎንቴ ከዲፖርቲቮ አላቬስ ጋር ተለያይተው ለ18 ወራት ያለ ስራ የተቀመጡበት ነበር።

ዴላፎንቴ በወቅቱ በፌዴሬሽኑ ውስጥ ይሰሩ የነበሩትን ኢኛኪ ሳኤዝን በስልክ ያነጋገሩ ሲሆን፤ ሳኤዝም ሀሳቡን ደግፈው ለእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ጥቆማ ሰጡ።

በወቅቱ የፌዴሬሽኑ የቅጥር ኃላፊ የነበሩት ጊኔስ መሌንዴዝ ከዴላፎንቴ ጋር ማድሪድ ውስጥ ከተወያዩ በኋላ ለ3 ወራት በሚቆይ አጭር የሙከራ ጊዜ ውል የእድሜ እርከን ቡድኑ አሰልጣኝ አድርገው ቀጠሯቸው።

ሉዊስ ዴላፎንቴ በጋዜጣ በወጣ ክፍት የስራ ቦታ ማስታወቂያ እግራቸው የስፔን እግር ኳስ ፌዴሬሽን ደጅ ደረሰ።

የዴላፎንቴን የሕይወት ታሪክና ውጣ ውረድ በመጽሐፍ መልክ ያዘጋጀው ኤድዋርድ ቨርዱ በወቅቱ የነበረውን ሁነት ሲገልጽ፤ “እሱ የመጣው  በጊዜያዊ  ውል እና በብሔራዊ ቡድኑ ውስጥ ያለው ቆይታ በማንኛውም ሰዓት ሊያበቃ ይችላል በሚል ስሜት ነበር” ሲል የዴላፎንቴን የመጀመሪያ ቅጥር ያስታውሰዋል።

ዴላፎንቴ የተወለደው በሰሜናዊ ስፔን በላ ሪዮሃ ግዛት በምትገኘው ሃሮ ከተማ ነው።

የዚህች ከተማ ነዋሪዎች የወይን አምራች አርሶ አደር በመሆናቸው እንግዳ ተቀባይነታቸው እና ባህላዊ እሴትን የሚያከብሩ መሆናቸው ይነገራል።

በፈረንጆቹ 2015 ከ19 ዓመት በታች እንዲሁም በ2019 ደግሞ ከ21 ዓመት በታች የስፔን ብሔራዊ ቡድንን የአውሮፓ ዋንጫ አሸናፊ አድርጓል።

በመቀጠል በ2020 በቶኪዮ ኦሊምፒክ ስፔን የብር ሜዳሊያ እንድታገኝ ትልቅ ስራን ሰርቶ አቅሙን አሳይቷል።

በ2022 የኳታር ዓለም ዋንጫ ስፔን በሞሮኮ በመለያ ምት ተሸንፋ ከውድድሩ በመሰናበቷ ሉዊስ ኤንሪኬ ከኃላፊነታቸው ሲነሱ በእድሜ እርከን ብሔራዊ ቡድኖች ውጤታማ የሆኑት ዴላፎንቴ ተረኛው የስፔን ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ሆኑ።

አሁን ግን ኃላፊነቱ የተሰጣቸው ከተሻለ ደሞዝ ጋር ሲሆን፤ ብሔራዊ ቡድኑን የተሻለ ውጤታማ ማድረግ እንዳለባቸው ከሚገልፅ ማሳሰቢያ ጋር ነበር።

ከኤንሪኬ ቡድኑን በኃላፊነት በተረከቡ በጥቂት ወራት ውስጥ ክሮሺያን በመለያ ምት በማሸነፍ ስፔን ከ11 ዓመታት በኋላ የመጀመሪያውን ትልቅ ዋንጫ እንድታገኝ አደረጉ።

በ2024 በጀርመን በተካሄደው የአውሮፓ ዋንጫ ስፔንን ሻምፒዮን ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡

በ2026 ዓለም ዋንጫ የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ የመድረኩን ጠንካራ ብሔራዊ ቡድን ፈረንሳይን ከጨዋታ ብልጫ ጋር በማሸነፍ ስፔንን ከ16 ዓመታት በኋላ የዓለም ዋንጫ ፍጻሜ አድርሰዋል።

ድንገት ባነበቡት የጋዜጣ ማስታወቂያ የስፔን ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝነት ስራቸውን የጀመሩት ሉዊስ ዴላፎንቴ ስፔንን የዓለም ዋንጫ አሸናፊ ያደርጉ ይሆን የሚለው ይጠበቃል፡፡

ስፔን የፍጻሜ ጨዋታዋን ነገ ምሽት 4 ሰዓት ላይ ከአርጀንቲና ጋር ታደርጋለች፡፡

በእንዳልካቸው ወዳጄ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.