የትግራይን ሕዝብ ለግል ጥቅሙ መያዣ ያደረገው ሕገ-ወጡ ቡድን
ሕገ-ወጡ የሕወሓት ቡድን በፕሪቶሪያው ስምምነት የተገኘውን ሰላም ከማጽናትና ህዝቡን ተጠቃሚ ከማድረግ ይልቅ፣ በድጋሚ ጦር መስበቅ ጀምሯል።
የፌዴራል መንግሥት በተደጋጋሚ የሰላም ጥሪ ቢያቀርብም፣ ቡድኑ የትግራይን ሕዝብ መያዣና ታጋች በማድረግ በክልሉ የውጭ ሃይሎችን ጭምር በመጋበዝና በመላላክ የጦርነት ያለህ እያለ ነው።
ይህም ትግራይን የጦርነት አውድማ የሚያደርግና ሕዝቡን ወደ ሌላ እልቂት የሚያመራ በመሆኑ ስጋት ፈጥሯል።
የክልሉ ነዋሪም ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ የትግራይን ለቅቆ እየወጣ ይገኛል።
ሕገ-ወጡ ቡድን ሥልጣኑን ለማስጠበቅ ሲል በክልሉ ወንዶችና ታዳጊ ወጣቶችን በግዳጅ በማሰርና በማጎሪያ ካምፖች በማገት ለውትድርና እያሰለጠነ ይገኛል።
ይህ ድርጊት የቀድሞው ጥፋት ሳያንሰው አዲስ ትውልድ ወደ ጦርነት የሚማግድ በመሆኑ ከፍተኛ ተቃውሞ አስነስቷል።
ቡድኑ ከሰብአዊነት ይልቅ ጥቅሙ ስለበለጠበት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተፈናቃዮችን አግቶ በመያዝ ድጋፍ እንኳን እንዳያገኙ አድርጓል
ይህ ሳያንሰው የፌዴራል መንግሥት ለክልሉ ህዝብ የሚያቀርበውን ውስን ሀብትና የነዳጅ አቅርቦት ለጦርነት ዝግጅት እያባከነ ይገኛል።
ይህም ሕዝቡን ከመደበኛ ልማት እና እርዳታ አግዶታል።
ቡድኑ በሕገ-ወጥ መንገድ ባካሄደው 14ኛው ጉባኤ ምክንያት በምርጫ ቦርድ እውቅና የተነፈገው ሲሆን፣ ይህም በሕግ ፊት እንደ አንድ ሕጋዊ የፖለቲካ ድርጅት የመንቀሳቀስ መብቱን ሙሉ በሙሉ አሳጥቶታል።
ሕገ-ወጡ ቡድኑ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደርን በማፍረስ በክልሉ ራሱ ፈላጭ ቆራጭ ለመሆን እየጣረ ይገኛል።
ይህም የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት በቀጥታ የሚጥስ ድርጊት ነው።
የቡድኑ ሕገ-ወጥነት ያንገሸገሻቸው የትግራይ ተወላጆች ትናንት በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ “አፈና ይቁም፤ ሰላም ይስፈን” በሚል መሪ ቃል ሰላማዊ ሰልፍ አካሂደዋል።
በሰልፉም ሕገ-ወጡ ሕወሓት የትግራይን ሕዝብ ከኢትዮጵያ ወንድም እህቶቹ ለመነጠል እና ሀገሪቱን ከባዕዳን ጋር በመሆን ወደ ጦርነት ለማምራት የሚያደርገውን ጥረት ተቃውመዋል።
የቀድሞው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት እና የጠቅላይ ሚኒስትሩ የምስራቅ አፍሪካ አማካሪ አቶ ጌታቸው ረዳ በሰልፉ ላይ ተገኝተው እንደገለጹት፣ ሕገ-ወጡ ቡድን የትግራይን ሕዝብ ወደ ኋላ እየጎተተና ለገዛ ሥልጣኑ ሲል የጦርነት ከበሮ እየደለቀ ይገኛል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት በትግራይ አካባቢ ሰላምን የሚያደፈርሱ እና የጦርነት ቅስቀሳ በሚያደርጉ በሕገወጡ የሕወሓት መሪዎችና ቤተሰቦቻቸው ላይ የቪዛ ማዕቀብ መጣሉ አይዘነጋም።
ይህም ማኅበረሰቡ የጥፋት ቡድኑን እንዲያገል ያሳየው ግልጽ ምልክት ነው።
በቡድኑ እገታ ከሃምሳ ዓመታት በላይ የተሰቃየው የትግራይ ሕዝብ አሁን የሚፈልገው ጦርነት ሳይሆን ሰላም፣ ልማት፣ መልሶ መቋቋምና ሁለንተናዊ ብልጽግና ነው።