Fana: At a Speed of Life!

ከበርካታ ኢትዮጵያውያን ብሔሮች ጋር ዝምድናን የፈጠረው ቤተሰብ በጎንደር

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 12፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ብላታ አሳየህኝ ወልደጊዮርጊስ ይባላሉ፡፡ በጎንደር ከተማ በተለምዶ ፊት ሚካኤል በሚባል አካባቢ ይኖሩ የነበሩ ጉምቱ አባት ናቸው።

በእንግዳ አቀባበሏ የምትታወቀው ጎንደር በተለያየ ምክንያት ወደ ከተማዋ የሚመጡ ኢትዮጵያዊያንን በእንግድነት ብቻ አይደለም የምታስተናግዳቸው፡፡ በደም እንደተሳሰረ እና እንደተዋለደ የቤተሰብ አባል ታደርጋለች እንጂ፡፡

ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች የመጡ ተማሪዎችን ከከተማዋ ነዋሪዎች ጋር ቤተሰብ እንዲሆኑ ያደረገው “የቃል ኪዳን ቤተሰብ” ጥረት ተጠቃሽ ነው፡፡

የብላታ አሳየህኝ ወልደጊዮርጊስ ታሪክ ደግሞ ከዚህ ከፍ ያለ ተሞክሮን ያሳየ ነው፡፡ እሳቸው ከ1 ሺህ በላይ አባላት ያሉት ቤተሰብ መስራች ናቸው፡፡ ከብላታ አሳየህኝ ወልደጊዮርጊስ በተገኙ 5 ቀዳሚ ትውልዶች የተጀመረው የቤተሰቡ የዘር ሐረግ አሁን 8ኛ ትውልድ ላይ ደርሷል፡፡ የቤተሰብ አባላቱ ከጎንደር ከተማ አልፎ በመላው አለም ጭምር ተሰራጭተው ይኖራሉ።

ዛሬ ይህ የቤተሰብ አባላት እርስ በርስ እንዲተዋወቁ፣ እንዲቀራረቡ እና ብዛት እንዳያራርቃቸው በሚል በቀደመው የብላታ አሳየህኝ ግቢ ለመሰባሰብ በቅቷል።

አቶ ሲሳይ አስማረ ዘሪሁን የአቶ አሳየህኝ የሶስት ትውልድ ልጅ ናቸው። የዘመድ አዝማዱ መተሳሰብና ፍቅር ከራስ አልፎ ሌሎችንም በትዳር ያጋመደ ሆኗል ይላሉ።

ከአቶ አሳየህኝ የዘር ሐረግ የተወለዱ የልጅ ልጆች ከተለያዩ ብሔሮች ተወላጆች ጋር ትዳር የመሰረቱ በፍቅርና መካባበር መርህ በኢትዮጵያዊነት ማዕቀፍ የሚኖሩ ናቸው።

ዕለተ እሑድ ሐምሌ 12 ቀን 2018 ዓ.ም ለአቶ አሳየህኝ የልጅ ልጆች የተለየች ቀን ናት፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ተራርቀው የነበሩ እንዲቀራረቡ፣ የማይተዋወቁ እንዲተዋወቁ፣ ሰብስብ ብለው ናፍቆታቸውን የገለጹበትና ቤተሰብነታቸውን ያጠናከሩበት ዕለት በመሆኑ።

ወጣት አብይ በትሩ ትናንት በተመሰረተው ብዙዎች ፍቅራችንና ቤተሰባዊ ትስስራችን እንደነሱ በሆነልኝ በሚሉት ቤተሰብ ውስጥ ያደገ ልጅ ነው። አሁን አሁን ግላዊ የኑሮ ይትባሃል በርካቶችን በሚፈትንበት በዚህ ዘመን፣ በአቶ አሳየህኝ የልጅ ልጆች ዘንድ ግን መራራቅ ብሎ ነገር የማይታሰብ እንደሆነ ይናገራል።

የቤተሰብ የዘር ሐረግን በውል ለመረዳት፣ በሐዘንና ደስታ አብሮ ለመሆን እና ለመደጋገፍ ዓላማ ያደረገው የአብሮነት ጉዞ ወደ ፊትም የተሻለ ሕልምን ያነገበ ነው።

ቤተሰቡ ከመተዋወቅ እና ከመደጋገፍ ባለፈ ወደፊት መላውን የቤተሰብ አባላት ያማከሉ ትልልቅ ፕሮጀክቶችን ወደ ሥራ ለማስገባት አስበናልም ነው ያለው ወጣት አብይ።

ትናንት በቅድመ አያቶቻቸው የተገነባውን ቤተሰባዊ ፍቅርና መከባበር ዛሬም ለዚህ ዘመን ልጆች ያስፈልገናል ያሉ የቤተሰቡ አባላት ከዓመታት ፍለጋ በኋላ የልባቸው መሻት ሰምሮ በላቀ ፍቅርና መተሳሰብ ለማዝለቅና ለማሻገር ረጅሙን ጉዞ ጀምረዋል።

በሕብር የተዋበውና የተጋመደው የብላታ አሳየህኝ ወልደጊዮርጊስ ቤተሰብ ስብስብ ለኢትዮጵያ ሕብረብሔራዊ አንድነት ተምሳሌት የሚሆን የተኖረ እና እየተኖረ ያለ አብነት ነው፡፡

በምናለ አየነው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.