Fana: At a Speed of Life!

29 ሚሊየን ሔክታር በማልማት 1 ነጥብ 3 ቢሊየን ኩንታል ምርት ተገኘ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 12፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በተጠናቀቀው 2018 በጀት ዓመት 29 ሚሊየን ሔክታር መሬት በማልማት 1 ነጥብ 3 ቢሊየን ኩንታል ምርት ተገኝቷል አሉ የግብርና ሚኒስትር አዲሱ አረጋ፡፡

የግብርና ሚኒስቴር እና የተጠሪ ተቋማት የሥራ ሃላፊዎች የግብርና ዘርፉን የ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ገምግመዋል፡፡

አቶ አዲሱ አረጋ በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በግብርናው ዘርፍ በስኬት የሚጠቀሱ ውጤቶች ተመዝግበዋል፡፡

በምርት ዘመኑ 29 ሚሊየን ሔክታር መሬት በማልማት 1 ነጥብ 3 ቢሊየን ኩንታል ምርት ማግኘት መቻሉን አብራርተዋ

አሁን ላይ 13 ሚሊየን ሔክታር መሬት በኩታ ገጠም መልማቱን ጠቁመው ÷ ይህም ምርታማነትን ለማሳደግ ትልቅ አቅም እንደፈጠረ ተናግረዋል።

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የግብርናው ዘርፍ 4 ነጥብ 55 ቢሊየን ዶላር ገቢ አስገኝቷል ያሉት ሚኒስትሩ ÷ ከዚህ ውስጥ ቡና 3 ነጥብ 1 ቢሊየን ዶላሩን እንደሚሸፍን ጠቁመዋል።

ከግብርና ግብዓት አቅርቦት አንጻር በርካታ ብልሹ አሰራሮችን በማስተካከል መንግሥት 80 ቢሊየን ብር ድጎማ አድርጎ ለበጀት ዓመቱ በቂ የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ ማሰራጨት መቻሉን አመልክተዋል፡፡

ከግብርና ሜካናይዜሽን አጠቃቀም ጋር በተያያዘ ከጊዜ ወደ ጊዜ ፍላጎቱና ተጠቃሚነቱ እያደገ በመምጣቱ አበረታች ለውጦች ተመዝግበዋል ነው ያሉት፡፡

በሌማት ትሩፋት ኢኒሼቲቭ በተከናወኑ ሥራዎች በእንስሳት ሃብት ልማት ስራ ከ4 ነጥብ 9 ሚሊየን በላይ እንስሳትን በሰው ሰራሽ ዘዴ ማዳቀል መቻሉን አብራርተዋል።

በአረንጓዴ ዐሻራ በዓመቱ ከ20 ሚሊየን በላይ የሰው ሃይልን በማስተባበር ከ8 ቢሊየን በላይ ችግኞችን ለመትከል ስኬታማ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው ማለታቸውንም የሚኒስቴሩ የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈጻሚ ይመር ዳውድ ለፋና ዲጂታል ገልጸዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.