መድን ፈንዱ ዜጎች በባንኮች ገንዘባቸውን ያለስጋት እንዲያስቀምጡ መተማመኛ ይሰጣል – ደሳለኝ አምባው (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 12፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የተቀማጭ ገንዘብ መድን ፈንድ ዜጎች በባንኮችና ማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ገንዘባቸውን ያለስጋት እንዲያስቀምጡ መተማመኛ ይሰጣል አሉ የፈንዱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ደሳለኝ አምባው (ዶ/ር)።
ዋና ሥራ አስፈጻሚው ከፋና ፖድካስት ጋር ባደረጉት ቆይታ ÷ የፈንዱ ዓላማ በባንኮችና ማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት የመውደቅ ችግር ቢያጋጥም አስቀማጮች በሕጉ መሠረት ካሳ እንዲያገኙ ማድረግና የፋይናንስ ሥርዓት እንዲረጋጋ አስተዋጽኦ ማበርከት ነው ብለዋል።
የመድን ፈንዱ ተጠሪነቱ ለብሔራዊ ባንክ መሆኑን ጠቅሰው÷ ዜጎች በባንኮች እና አነስተኛ የፋይናንስ ተቋማት በሚያስቀምጡት ገንዘብ እምነት እንዲኖራቸው በማድረግ በኩል ከፍተኛ ሚና እንዳለው አብራርተዋል፡፡
ከልማት ባንክ ውጭ ሁሉም ባንኮች እና ማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት የመድን ፈንዱ አባል ናቸው ያሉት ደሳለኝ (ዶ/ር) ÷ ከአባል ተቋማት 23 ቢሊየን ብር የሚጠጋ አረቦን መሰብሰብ መቻሉን ተናግረዋል፡፡
ከተሰበሰበው አረቦን ውስጥ 21 ቢሊየን የሚጠጋው ብር የተሰበሰበው ከመደበኛ ተቀማጭ ገንዘብ ሲሆን ÷ ቀሪው ከወለድ ነጻ ተቀማጭ ገንዘብ መሆኑን አንስተዋል፡፡
ከገንዘብ አስቀማጮች 97 በመቶ የሚሆኑት ከ100 ሺህ ብር በታች ያስቀመጡ መሆናቸውን የጠቀሱት ሥራ አስፈጻሚው÷ የመድን ፈንዱ ለአነስተኛ ገንዘብ አስቀማጮች ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸዋል፡፡
ከሁሉም አባል የንግድ ባንኮችና አነስተኛ የገንዘብ ተቋማት 0 ነጥብ 3 ከመቶ አረቦን እንደሚሰበሰብ ጠቁመው÷ በተቋማቱ ችግር ቢያጋጥም የመድን ፈንዱ ከከፋይ ባንክ ጋር ስምምነት በመፍጠር ክፍያ እንደሚፈጸም ተናግረዋል፡፡
በሠራዊት ሸሎ
የተቀማጭ ገንዘብ መድን ፈንድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ደሳለኝ አምባው (ዶ/ር) ከፋና ፖድካስት ጋር ያደረጉትን ቆይታ ለመከታተል ማስፈንጠሪያውን ይጫኑ፡- https://www.youtube.com/watch?v=ctA5zNsCw8M