Fana: At a Speed of Life!

ከጦርነት አዙሪት መውጣት የማይችለው ሕገ ወጡ ህወሓት

የኢትዮጵያ ሕዝብ ከግጭትና የጥፋት ሁኔታ ውስጥ ወጥቶ ሰላምን፣ ልማትንና አንድነትን አጥብቆ እየሻተ ባለበት ወቅት የትግራይ ክልል ሕዝብና ወጣቶችም የሰላምን አስፈላጊነት በተግባር እያረጋገጡ ይገኛል።

ሕገ ወጡ የህወሓት ቡድን የሰላም መንገዶችን በመዝጋትና የስልጣን ጥሙን ለማርካት ሲል ወጣቱን ዳግም ወደ ጦርነት ለመማገድ ቢሞክርም ሕዝቡ ይህን አፍራሽ አካሄድ በጽኑ እየተቃወመ ነው።

የትግራይ ወጣቶች ካለፉት ዓመታት የጦርነት ሰቆቃ በመማር ለጥቂቶች ጥቅምና የስልጣን ጥም ተብሎ ሕይወታቸውን ላለመገበር ፅኑ አቋም ወስደዋል።

በግዴታ ወደ ጦርነት የሚደረግ አፈሳን አጥብቀው በማውገዝ ከቀሪው የኢትዮጵያ ወንድሞቻቸው ጋር ያላቸውን ታሪካዊና ሀገራዊ ትስስር በማጠናከር የሰላምና የልማት ተምሳሌት ለመሆን ጥረት ጀምረዋል።

የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ዕድገት ለመግታት እና ሀገሪቱን በትርምስ አዙሪት ውስጥ ለመጣል የሚደክሙ የውስጥ ባንዳዎችና የውጭ ጠላቶች ሴራ በተግባር እየመከነ መጥቷል።

በሕገ ወጡ ቡድን የስልጣን ጥም የተነሳ የትግራይ ክልል ሕዝብ የሚያስፈልገው የልማት ጥያቄ ምላሽ እንዳያገኝ ከኢትዮጵያ ጠላቶች ጋር እየሰራ ቢሆንም ይህ የኖረበት የጥፋት መንገድ በትግራይ ክልል ህዝብ ዘንድ እየገጠመው ያለው ብርቱ ተቃውሞ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም መረጋገጥ ተስፋ ነው።

በአሁኑ ወቅት የህወሓት ቡድን የጦርነት ወሬ በማናፈስ፣ ህዝብን በማስፈራራት እና አፋኝ ሕጎችን በመደንገግ የትግራይን ህዝብ ለከፍተኛ መከራና ግፍ ዳርጓል።

ቡድኑ የወንጀል ድርጊቱን የሚደግፍ ህግ በመደንገግ ትግራይን በሁከትና በቀውስ ውስጥ ለማቆየት እየተንቀሳቀሰ ሲሆን፤ ለጦርነት ዓላማው በዚህ በደነገገው ህግ ወጣቶችን እያፈሰ ነው።

ይህንን ጨምሮ የቡድኑን የወንጀል ድርጊቶች የሚቃወም ሰላማዊ ሰልፍ ‘አፈሳ ይቁም፤ ሰላም ይስፈን’ በሚል መሪ ሀሳብ ትናንት በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ ተካሂዷል።

ሰላማዊ ሰልፉን ያዘጋጀው የትግራይ ሰላምና ለውጥ ምክር ቤት፤ ህገ ወጡ የህወሓት ቡድን ከመሰሎቹ አሸባሪ ኃይሎች ጋር ተጣምሮ ኢትዮጵያን ጨምሮ ቀጣናውን ለማተራመስ እየሰራ መሆኑን አስታውቋል።

ሕገ ወጥ ቡድኑ ቀጣናውን የማያባራ ቀውስ ውስጥ ለመክተት እየሰራ ነው።

ቡድኑ ከመሰሎቹ የኢትዮጵያ ጠላት ከሆኑ በቀይ ባሕር ዳርቻ ከሚገኙ አሸባሪ ኃይሎች ጋር ተሳስሮ በመስራት ላይ ሲሆን፤ የትግራይ ወጣቶችን አስታጥቆ በኤርትራ በረሃዎች አሳልፎ ለሱዳን ጦርነት ለሽያጭ አቅርቦ እያዋጋ ነው።

በቡድኑ እየተፈጸመ ባለው አፈና እናቶች በጦርነት ያጧቸውን ልጆቻቸው ሐዘን እንኳን ሳይወጡ፤ የቀሩትን ልጆቻቸውን ለማዳን ድምጻቸውን በማሰማት ላይ ናቸው።

ይሁን እንጂ ይህ ህገ ወጥ ቡድን ለእነዚህ እናቶች ሰብዓዊ መብት ከመቆርቆር ይልቅ ድብደባ በመፈጸም እና ጥይት በመተኮስ ከፍተኛ ጥቃት እያደረሰባቸው ይገኛል።

በተለይም ወጣቶችን በግዳጅ እያፈሱ ወደ ኤርትራ እና ሱዳን ድንበር እያጋዘ የሚገኘው ይህ ህገወጥ አካሄድ፣ በሕዝቡ ላይ እየደረሰ ያለውን ሰቆቃ እጅግ አሳሳቢ አድርጎታል።

የቡድኑ ሕልውና በሙስና እና በዘረፋ የተሳሰረ በመሆኑ ከስልጣን ውጭ መሆንን እንደ አደጋ በመቁጠር የሰላም ሒደቱን ለማደናቀፍ እየሠራ ይገኛል።

ወጣቶችን እያፈሰ ወደ ኤርትራ እና ሱዳን እያጋዘ የሚገኘው ህገወጥ ቡድን የሚፈጽመውን ድርጊት በቃ ማለት ይገባል።

ትናንት በአዲስ አበባ የተካሄደው በትግራይ ሕዝብ ላይ እየተፈጸመ ያለውን አፈና እና ጭቆና የሚያወግዝ እንዲሁም የጦርነት ዝግጅትን የሚቃወም ሰላማዊ ሰልፍ ስኬታማ እንደነበርም የትግራይ የሰላምና ለውጥ ምክር ቤት አስታውቋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.