Fana: At a Speed of Life!

አረንጓዴ ዐሻራ ለትውልድ የተሻለ ዓለም የማውረስ ትልም

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 13፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በምንኖርበት ክፍለ ዘመን ዓለማችን ካጋጠሟት ታላላቅ ፈተናዎች መካከል የአየር ንብረት መዛባት፣ የበረሃማነት መስፋፋት እና የውሀ ሀብት መንጠፍ በአጠቃላይ የተፈጥሮ ሀብቶች መመናመን በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳሉ።

ኢትዮጵያም የዚህ ዓለም አቀፋዊ ቀውስ ገፈት ቀማሸ ከሆኑ ሀገራት አንዷ ነች።

ይህንን ዓለም የተጋረጠባትን ትልቅ ፈተና ለመሻገር የተለያዩ ጥረቶች ሲደረጉ ቆይተዋል፤ ምንም እንኳን የሰው ልጅ ተፈጥሮ ላይ ላደረሰው ህመም ፈውስ በአፋጣኝ መስጠት ባይቻልም ሙከራዎች እዚህም እዛም መደረጋቸው ግን አልቀረም ነበር፡፡

ይህንን ታሪካዊ ፈተና ለመቀልበስና ተፈጥሮን በጤና ለትውልድ ለማድረስ፤ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አረንጓዴ ዐሻራ በሚል ስያሜ በሀገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረው መርሐ-ግብር ታላቅ ብሔራዊ ንቅናቄን ፈጥሯል።

ይህ ንቅናቄ ተራ ችግኝ የመትከል ተግባር ሳይሆን የሀገርን ሁለንተናዊ ገጽታ፤ ስነ-ምህዳር፣ ኢኮኖሚና ማህበራዊ ህይወትን የቀየረ ዘላቂ የልማት ስትራቴጂ ነው።

የዚህ ታላቅ ትልም ትሩፋቶችም ከምድር በላይ ካለው አረንጓዴነት ባሻገር ከርሰ-ምድርን ማበልጸግ ድረስ በጥልቀት ይሰራሉ።

የአረንጓዴ ዐሻራ ቀዳሚና ዋነኛው ትኩረት የተፈጥሮ ሚዛንን መልሶ ማስጠበቅ ነው። ላለፉት እልፍ ዘመናት በደን መጨፍጨፍ ምክንያት የደረሰውን ተፈጥሯዊ ውድመት እንዲያገግም በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል።

በየዓመቱ በቢሊየን የሚቆጠሩ አዳዲስ ችግኞችን በመትከልና በመንከባከብ የሀገሪቱን የደን ሽፋን አስደናቂ በሚባል ፍጥነት ማሳደግ ተችሏል፡፡

የጠፉ ደኖች መመለሳቸው መሸሸጊያ አጥተው ተሰድደው የነበሩ የዱር እንስሳት፣ አእዋፋትና ሌሎች ፍጡራን ወደ ቀድሞ መኖሪያቸው እንዲመለሱ በማድረግ፤ የተፈጥሮን የምግብ ሰንሰለት ጠብቆ ለማቆየት ረድቷል።

ኢትዮጵያ በየዓመቱ በጎርፍ ምክንያት በቢሊየን ቶን የሚቆጠር ለም አፈር ተሸርሽሮ ድንበሯን አቋርጦ ይሄድ ነበር፡፡

በአረንጓዴ ዐሻራ የተተከሉ ዛፎች ስር አፈርን አጥብቀው እንዲይዙ በማድረግ የመሬት መደርመስና መሸርሸርን ቀንሰዋል።

ከዚህም በላይ ዝናብ በሚዘንብበት ወቅት ውሃው መሬት ውስጥ ሰርጎ እንዲገባ በማድረግ የከርሰ-ምድር ውሃን መጠንን ከፍ ማድረግ ተችሏል። በዚህም ሳቢያ በበርካታ የሀገሪቱ ክፍሎች ነጥፈው የነበሩ ምንጮችና ወንዞች ህይወት መዝራት ጀምረዋል።

እጽዋቶች ከባቢ አየርን የሚበክለውን ካርቦን ዳይኦክሳይድን በመውሰድ ኦክስጅንን ወደ ከባቢ አየር ይለቃሉ። የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ-ግብር ሀገሪቱ የዓለም ሙቀትን ለመቀነስ የምታደርገውን ጥረት በተግባር ያሳየ ሲሆን፣ በአካባቢው የሚስተዋለውን ከፍተኛ ሙቀትና የድርቅ አዝማሚያ ለመቀነስ ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክቷል።

መርሐ-ግብሩ ከተራ ዛፎች ባለፈ ለምግብነትና ገቢ ምንጭነት የሚያገለግሉ የፍራፍሬ ችግኞችን በስፋት ማካተቱ፤ አርሶ አደሩም ሆነ የከተማው ነዋሪ የጓሮ አትክልትና ፍራፍሬን በማምረት፣ የቤተሰብ የአመጋገብ ስርዓትን እንዲያሻሽልና ተጨማሪ ገቢ እንዲያገኝ አስችሏል።

ከዚህ ጋር ተያይዞም የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ፤ አዳዲስ የስራ እድሎችን በመፍጠር የማህበረሰቡን ኢኮኖሚ ማሻሻል አስችሏል፡፡

አረንጓዴ ዐሻራ ችግኝ የመትከል መርሀ-ግብር ብቻ ሳይሆን ለትውልድ የተሻለን ዓለም የማውረስ ትልም ነው፡፡

የዘንድሮው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር “ተስፋን እንትከል” በሚል መሪ ቃል እየተካሄደ ይገኛል፡፡

በመልካም ፈቃዱ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.