ኢትዮጵያ የዱር ህይወት ጥበቃን ለትውልድ በማሻገር ከአፍሪካ ግንባር ቀደም ናት – ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 14፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ ኢትዮጵያ ለዘመናት ያከማቸችውን የዱር ሕይወት ጥበቃ ከትውልድ ወደ ትውልድ በማሸጋገር ረገድ ከአፍሪካ ግንባር ቀደም ናት አሉ።
የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሥልጣን 60ኛ ዓመት የምሥረታ በዓል “60 ዓመታትን ለኢትዮጵያ የዱር ሕይወት” በሚል መሪ ሐሳብ በአዲስ አበባ ተከብሯል።
ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ የኢትዮጵያውያን የዱር ሕይወት ጥበቃ ባህላዊ ሥርዓት ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፍ አስደናቂ ዕሴት ነው፡፡
የኢትዮጵያ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር የሥነምኅዳር ደኅንነትን በመጠበቅ የዱር ሕይወት መጠጊያና መኖሪያ የሚያገኙበትን ወሳኝ ዕድል ፈጥሯል ብለዋል።
በሀገራዊ ለውጡ ማግስት ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ የተፈጥሮ ሀብቶችንና የብዝኃ ሕይወት ሥነምኅዳር ሚዛንን ለመጠበቅ በርካታ ተግባራት መከናወናቸውንም አንስተዋል።
የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት መለያ የሆነው የዋሊያ አይቤክስ መመናመን አሳሳቢ ነው ያሉት ፕሬዚዳንቱ፥ ይህንን መታደግ ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ግዴታችን ነው ብለዋል፡፡
በብሔራዊ ፓርኮች ልማት አዲስ ሕይወትና እይታ ለመስጠት የተደረገው ርብርብ ትልቅ እመርታ ማስመዝገቡንና የሀገር ውስጥና የውጭ ጎብኚዎችን ለመሳብ ለሚደረገው ጥረት ቁልፍ እየሆነ መምጣቱን አመልክተዋል።
በከተሞች እየተገነቡ ያሉ ፓርኮችም ሕብረተሰቡ ለዱር ሕይወት ያለውን የእውቀት አድማስ እንደሚያሰፉ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡