በወጣቶች ተቃውሞ የገጠመው የህገ ወጡ ህወሓት የአፈሳ ወንጀል
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 14፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ህገ ወጡ የህወሃት ቡድን የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት በግልጽ በመጣስ በትግራይ ክልል ወጣቶች ላይ እየፈጸመ ያለው የግዳጅ አፈሳ፣ የእስራት እና የጭቆና ድርጊት ሊቆም ይገባል አሉ ከአፈሳው ያመለጡ የክልሉ ተወላጆች።
ወጣቶቹ ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን እንዳሉት፥ ቡድኑ ወጣቱን ትውልድ ለስልጣን ማራዘሚያና ለጦርነት ማገዶነት እየተጠቀመበት መሆኑ ክልሉን ለከፍተኛ ማህበራዊ ቀውስ ዳርጎታል።
ከቡድኑ አፈሳ ማምለጥ የቻለው ጸጋልዑል በርሄ ቡድኑ ወጣቶችን ያለፍላጎታቸው ከቤተክርስቲያን፣ ከትምህርት ቤትና ከተለያዩ አካባቢዎች በመኪና እያፈሰ ይወስዳል ብሏል።
ይህንን የግዳጅ አፈሳ በመቃወም “አንገደልም፣ ውጊያ አያስፈልገንም” በሚል ለማምለጥ የሞከሩ በርካታ ወጣቶች በሽሬ ከተማ በጥይት ተደብድበው መገደላቸውን ገልጾ፤ በህገ ወጡ ህወሓት እጅ የወደቁ ወጣቶች ታፍነው ወደ ሳዋ መላካቸውን ገልጿል።
በትግራይ ወጣቶች ላይ እየደረሰ ያለው ግፍ እጅግ የሚያሳዝንና ሊቆም የሚገባው መሆኑንም አጽንኦት ሰጥቷል።
አቶ መሃሪ ይስባ በበኩላቸው ህገወጡ ቡድን በክልሉ እስከ 500 ሺህ ብር ቅጣትና እስከ ሞት ፍርድ የሚደርስ ህግ አውጥቶ ህዝቡ እያሰቃየ ይገኛል ነው ያሉት።
በተለይም ወደ በረሃ የሸሸ ወጣት ካለ ቤተሰቦቹ በህገ ወጡ ቡድን ከባድ ቅጣት እንደሚጣልባቸው ገልጸው፤ እናቶችን ያለ ልጅ ካስቀረው የጥፋት ቡድን በመላቀቅ ወጣቱ ሰላም ሊያገኝ ይገባል ሲሉ አመልክተዋል።
በትግራይ ውስጥ ቡድኑን የተቃወመ አካል በጠላትነት እንደሚፈረጅ የገለጹት ደግሞ መምህር ገ/ኪሮስ ህሉፍ ናቸው።
የህገ ወጡ ቡድን በኃይል የመግዛት አካሄድ ወጣቱን ክፉኛ እያሰቃየው ይገኛል ያሉት።
የክልሉ ወጣቶች በአሁኑ ወቅት ዋና ፍላጎታቸው ጦርነት ሳይሆን ከሌሎች የኢትዮጵያ ወንድምና እህቶቻቸው ጋር በሰላም፣ በፍቅርና በደስታ መኖር እንዲሁም የልማት ተጠቃሚ መሆን ነው ሲሉ ተናግረዋል።