ሀገራዊ ምክክሩ የውጭ ጣልቃ ገብነትን ለማስቀረት ወሳኝ መድረክ ነው – አቶ ማስረሻ ሰጤ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 14፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ጠንካራ ሆና እንዳትወጣ የሚፈልጉ የውጭ ኃይሎችን ጣልቃ ገብነት ለማስቀረት ሀገራዊ ምክክሩ ወሳኝ መድረክ ነው አሉ የሰላም አማራጭን የተቀበሉት የምክክሩ ተሳታፊ አቶ ማስረሻ ሰጤ፡፡
በሰላማዊ መንገድ ለመታገል ከትጥቅ ትግል የተመለሱ የተለያዩ የታጠቁ ቡድኖች አመራሮችና አባላት በሀገራዊ ምክክር ጉባኤው ላይ በንቃት እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡
ከእነዚህ መካከል አንዱ የሆኑት አቶ ማስረሻ ሰጤ በምክክሩ ላይ እያደረጉ ያሉትን ተሳትፎ በተመለከተ በሰጡት አስተያየት፥ በዘመናት መካከል የሚገኝ ወሳኝ የምክክር ሂደት ተፈጥሯል ብለዋል፡፡
የግጭት አማራጭ ችግሮችን ለመፍታት የመጨረሻ ውጤት እንዳልሆነ ገልጸው፥ ይህ የምክክር መድረክ ለረጅም ጊዜ ስንፈልገው የነበረ ነው ብለዋል፡፡
በምክክሩ ላይ ከሁሉም የሕብረተሰብ ክፍሎች የተወከሉ ተመካካሪዎች የሕዝብ አጀንዳ ይዘው መቅረባቸውንና በሂደቱም በምክክርና በመደማመጥ ሁሉንም ኢትዮጵያውያን በእኩል ዐይን የምታይ ኢትዮጵያን ለመፍጠር ወሳኝ ምዕራፍ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
አሁን ላይ በትጥቅ ትግል የሚንቀሳቀሱ አካላት በባዕዳን አጀንዳ መጠለፋቸውን ያነሱት አቶ ማስረሻ፥ እነዚህ አካላት ይህንን ተገንዝበው ወደ ምክክሩ ሊመለሱ ይገባል ነው ያሉት፡፡
የውጭ ኃይሎችን ተልዕኮ መሸከም በሕዝቡ ላይ ጠባሳ የሚያሳርፍ በመሆኑ ከግጭት አዙሪት የሚወጣበትን ይህን የምክክር መድረክ በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
ሀገራችንን በግጭት ውስጥ በማቆየት ባዕዳን ጣልቃ እንዲገቡ በር ከመክፈት ይልቅ ችግሮቻችንን በንግግርና በመመካከር መፍታት ይገባናል ብለዋል፡፡
በኃይለማርያም ተገኝ