Fana: At a Speed of Life!

ባህር በር፤ የመጪውን ትውልድ ዕድል የማስጠበቅ ኃላፊነት

አዲስ አበባ፣ መስከረም 11፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የባህር በር ማግኘት ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ደኅንነት፣ የኢኮኖሚ ዕድገት እና የንግድ ነጻነት ወሳኝ መሠረት ነው፡፡
በመሆኑም የባህር በር ማጣቷ ለኢኮኖሚዋ፣ ለብሔራዊ ደኀንነቷ እና ለጂኦ ፖለቲካዊ ተጽዕኖዋ ትልቅ ማነቆ ሆኖ ቆይቷል።
እውነተኛ ብሔራዊ ደኅንነት የሚረጋገጠው ስትራቴጂካዊ ቁሳቁሶች ያለ ምንም የውጭ ጫና፣ እገዳ ወይም የጎረቤት ሀገራት ፍላጎት በቀጥታ ወደ ሀገር ውስጥ መግባት ሲችሉ ነው።
ለኢትዮጵያ የባህር በር ማግኘት የሕልውና እና የብሔራዊ ጥቅምን የማስከበር ቀዳሚ ጉዳይ ነው።
የተዘጉ የንግድ በሮች መከፈት አዳዲስ የኢንዱስትሪ እና የኢንቨስትመንት ዕድሎችን በመፍጠር የወጣቶችን የሥራ አጥነት ችግር ለመቅረፍ ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል።
አንድ ሀገር እንደ ሀገር የምትቀጥለው ብሔራዊ ጥቅሞቿን አስከብራ ስትኖር ብቻ ነው:: ብሔራዊ ጥቅም ከፓርቲ፣ ከመሪዎች፣ ከወቅታዊ መንግሥታት በላይ የሆነ ትውልድ እና ዘመን ተሻጋሪ የሀገር አጀንዳ ነው፡፡
ኢትዮጵያ በየጊዜው የምታወጣቸው ፖሊሲዎች፣ ስትራቴጂዎች እና ዕቅዶችም ከብሔራዊ ጥቅሞቿ የሚቀዱ ናቸው፡፡
አሁን ያለው ትውልድ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ፈተና የሆኑ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርጎ ለመፍትሔው መሥራት ይገባዋል፡፡
ለዚህም ውስጣዊ አንድነትን ማጽናት፣ ሰላም እና ደህንነትን ማረጋገጥ፣ የፖለቲካ ባሕልን ማዘመን፣ የሃሳብ ፖለቲካን ማስፈን፣ ከፖለቲካ ኃይሎች ጋር ሰላማዊ አማራጭ መከተል፣ ሀገራዊ መግባትን መፍጠር፣ የጋራ ትርክትን በጋራ ጥቅም ላይ መገንባት መፍትሔ ነው፡፡
በዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ፣ የባህር ጠረፍና የባህር ኃይል ያላቸው ሀገራት ያላቸው የድርድርና የፖለቲካ ተሰሚነት ከፍተኛ ነው። ቀጥተኛ የባህር በር መኖር ኢትዮጵያ በቀይ ባህርና በስትራቴጂካዊ የውሃ አካላት ዙሪያ በሚደረጉ ቀጣናዊ ውሳኔዎች ላይ ያላትን ድምጽ ከፍ ያደርጋል፡፡
ለኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ የመጪውን ትውልድ መብትና ዕድል የማስከበር የታሪክ ኃላፊነት ነው።
ሰላማዊ ዲፕሎማሲን፣ የዓለም አቀፍ የባህር ሕግጋትን እና የጋራ ተጠቃሚነትን መርህ በመጠቀም ኢትዮጵያ ወደ ዓለም የምትወጣበትን የራሷን በር ማረጋገጥ ትችላለች።
በአጠቃላይ አስተማማኝ የባህር በር ማግኘት ለኢትዮጵያ የረጅም ጊዜ ብልጽግና፣ መረጋጋት እና ለብሔራዊ ሉዓላዊነት ዋነኛው መሠረት ነው።
በትዕግስት ግዛቸው
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.