Fana: At a Speed of Life!

ለዘመናት ሲንከባለሉ የነበሩ ችግሮች ላይ በምክክር መግባባት ላይ መድረስ የኢትዮጵያን የወደፊት እጣ ፈንታ ብሩህ ያደርጋል

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 16፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ለዘመናት ሲንከባለሉ የነበሩ ችግሮች ላይ በምክክር መግባባት ላይ መድረስ የኢትዮጵያን የወደፊት እጣ ፈንታ ብሩህ ያደርጋል አሉ የአዳማ ከተማ ነዋሪዎች፡፡

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በ80 ንዑስ ቡድኖች ያደራጀው የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ የውይይት ምዕራፍ ተጀምሯል።

የተጀመረው የንዑስ ቡድን ውይይት የሀገራዊ ምክክሩ ቁልፍ ምዕራፍ ነው።

ከፋና ዲጂታል ጋር ቆይታ ያደረጉ የአዳማ ከተማ ነዋሪዎች፤ ምክክሩ የኢትዮጵያን የዘመናት ልዩነት እና ቁርሾ ይፈታል ብለዋል፡፡

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አሳታፊና አካታች በሆነ መንገድ ከኢትዮጵያውያን ያሰባሰባቸውን ጉዳዮች በስምንት ዋና ዋና አጀንዳ ለይቶ ለሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ማቅረቡን ገልጸው፤ ጉባኤው ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና ልማት መፍትሄ ይዞ እንደሚመጣ እምነታቸውን ገልጸዋል።

ለዘመናት ሲንከባለሉ የነበሩና የግጭት ምክንያት የነበሩ ጉዳዮች ላይ በመምከር መግባባት ላይ መድረስ የኢትዮጵያን የወደፊት እጣ ፈንታ ብሩህ ያደርጋል ነው ያሉት።

የተለዩት አጀንዳዎች በኢትዮጵያ በችግር ሲነሱ የነበሩ ጉዳዮችን አሟልተው የያዙ እጅግ ቁልፍ እና ወሳኝ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ በአጀንዳዎቹ ላይ የሚደረጉት ውይይቶች ውጤታማነት ለሀገር እድገት የጎላ ሚና እንዳለው አመልክተዋል።

አሁን ያለው ትውልድ ባለፉት ዓመታት በነበሩ የቤት ስራዎች ሲለያይና ሲቋሰል እንደነበር አስታውሰው፤ ይሄንን መጥፎ ታሪክ ለቀጣይ ትውልድ ማስተላለፍ አይገባም ብለዋል፡፡

በመሆኑም ቀጣዩ ትውልድ ተመሳሳይ እጣ ፋንታ እንዳይከተለው ሁሉም ዜጋ ለምክክሩ መሳካት የበኩሉን አስተዋጽኦ ማበርከት እንዳለበት አስገንዝበዋል።

ምክንቶችን እየፈጠሩ መለያየት እና ወደ ግጭት መግባት ትርፉ ድህነትና ኋላ ቀርነት ነው ያሉት ነዋሪዎቹ፤ ከዚህ በኋላ በአንድ ሀገር ጥላ ስር እንደሚኖር ዜጋ መተባበር ያስፈልገዋል ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ሙስና በመዋጋት እና ዴሞክራሲያዊ ባህልን በማጎልበት ለቀጣይ ትውልድ የበለጸገች እና ሰፊ እድሎች መገኛ የሆነች ሀገር መፍጠር አሁን ያለው ትውልድ ትልቅ የቤት ስራ ነው ብለዋል፡፡

በአቤል ነዋይ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.