የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 17፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ዓለማችን በአሁኑ ወቅት እያጋጠሟት ካሉ ትላልቅ ፈተናዎች መካከል የአየር ንብረት ለውጥ፣ የተፈጥሮ ሀብት መመናመን እና የአካባቢ ብክለት በዋናነት ይጠቀሳሉ።
እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ እና የአሁኑንም የቀጣዩንም ትውልድ ዓለም ለመኖር ተስማሚ ለማድረግ ሀገራት የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ እንደ ዋነኛ መፍትሄ በመውሰድ በመተግበር ላይ ይገኛሉ፡፡
አረንጓዴ ኢኮኖሚ በተፈጥሮ ስነምህዳር ላይ የሚከሰቱ ጥፋቶችን ብሎም በአየር ንብረት ላይ ሊከሰቱ የሚችሉ መዛባቶችን ለመከላከል የሚያግዝ ስትራቱጂ ነው፡፡
ስትራቴጂው እንደ ነዳጅ ያሉ ከባቢ አየርን የሚበክሉ የሀይል አማራጮችን በአረንጓዴ፤ ማለትም በፀሐይ ሀይል፤ በንፋስ፤ በጂኦተርማልና ሀይድሮ ኤሌክትሪክ የሀይል ምንጮች ባሉት መተካትን ያካትታል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ የከተሞችንና የኢንዱስትሪ ተረፈ ምርቶችን በአግባቡ በማስወገድና መልሶ ጥቅም ላይ በማዋል በውሀ አካላትና በአፈር ላይ የሚከሰት ብክለትን የሚከላከል የታዳሽ ሀይል አጠቃቀምን ይተገብራል፡፡
የተፈትሮ ሀብት መራቆትን ተከትሎ የሚከሰተውን የአየር ንብረት መዛባት ለመከላከል ተፈጥሮ እንዲያገግም የሚያደርጉ የደን ጥበቃና እንክብካቤ ብሎም የችግኝ ተከላ መርሀ-ግብሮችንም ይከውናል፡፡
የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ የመጨረሻ ግቡ ከካርቦን ልቀት ፈተና ነጻ የሆነች ዓለምን መፍጠር ነው። ይህ ማለት ወደ ከባቢ አየር የምንለቀው በካይ ጋዝ እና የተፈጥሮ ስነ-ምህዳሩ (ደኖች እና የውሀ አካላት) መልሰው የሚለግሱት ኦክሲጅን ተመጣጣኝ እንዲሆን ማድረግ ነው።
ኢትዮጵያም የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋም አረንጓዴ ኢኮኖሚ ስትራቴጂን እንደ አውሮፒያኑ የዘመን ቀመር በ2011 በመቅረጽ የካርቦን ልቀትን ሳትጨምር የኢኮኖሚ እድገቷን እውን ለማድረግ ቃል የገባች በዓለም አቀፍ ደረጃ ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ሀገር ለመሆን በቅታለች።
ኢትዮጵያ ይህንን ስትራቴጂ መተግበር ከጀመረች ሰንበትበት ያለች ሲሆን ከአረንጓዴ ዐሻራ መርሀ ግብር ጀምሮ አረንጓዴ የሀይል አማራጮችን መጠቀምና ታዳሽ ሀይል በስፋት ጥቅም ላይ እንዲውል በመስራት ላይ ትገኛለች፡፡
በመደመር መንግስት ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶበት በመከወን ላይ ያለው ይህ ስትራቴጂ አነስተኛ ወይም ዜሮ የካርቦን ልቀት መጠን ያላቸውን የሕዝብ ትራንስፖርቶችን በማበረታታትና በማስፋፋት ለእቅዱ ስኬት መንገድ በመጥረግ ላይ ይገኛል፡፡
ከፍተኛ የካርቦን ልቀት የሚደቅነውን አደጋ ለመታገል በከተሞች መሀል የተለያዩ አረንጓዴ ስፍራዎችን ከመፍጠር አኳያ ሰፋፊ ስራዎች በመሰራት ላይ ይገኛሉ፡፡
በዚህም አረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታን በመከተል ብልጽግናዋን በማረጋገጥ ላይ ያለች ግንባር ቀደም አፍሪካዊ ሀገር ያደርጋታል፡፡
ኢትዮጵያ ተግብራው እየተንቀሳቀሰችው ያለው ይህ ትልቅ ትልም ሲሳካ የምግብ ዋስትና ይረጋገጣል፣ የአየር ንብረት መዛባትን መከላከል ይቻላል፣ ኢኮኖሚው ዘላቂና አስተማማኝ መሰረት ይኖረዋል ብሎም ሀገሪቷ ለአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ባላት ቁርጠኝነት ለዓለም አየር ንበረት መስተካከል ትልቅ አስተዋጽኦን ታበረክታለች፡፡
በመልካም ፈቃዱ