የመደማመጥ ባሕል ለተሻለች ኢትዮጵያ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 18፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የምክክር መድረክ መነሻና መቋጫው ሀሳብ ነው፥ ሀገር የሚገነቡ ሀሳቦች በውይይት ቀርበው ወደ ጋራ ስምምነት ያደርሳሉ።
ለዚህም በገለልተኝነት የተቋቋመው የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሁሉንም የማህበረሰብ ክፍል ባማከለ መልኩ አጀንዳዎች የመሰብሰብ ሂደቱን አጠናቅቆ ስምንት ዋና ዋና አጀንዳዎችን በመለየት የምክክር ጉባኤ ምዕራፍ ላይ ይገኛል፡፡
ለዘመናት አብረውን የዘለቁ የማንስማማባቸውን ነገር ግን እያባበልን ተሸክመን ስንዞር የነበሩትን ችግሮች በመፍታት የተሻለች ሀገር የምንገነባበትን የምክክር መንገድ ተጀምሯል፡፡
ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲ፣ መግባባትና የጋራ ጥቅም ላይ የተመሠረተ አካሄድ የምትከተለው በውጭ ግንኙነቷ ብቻ አይደለም፤ በውስጥ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት፣ የጋራ አንድነትና ሰላምን በዘላቂነት ለማስጠበቅም ጭምር እንጂ፡፡
ህብረተሰቡ ጦርነትና ግጭት በቃኝ በማለት፣ ልጆቹ ለግዴታ ጦርነት መስዋዕት እንዳይሆኑ፣ በዜጎች ግብር የተሰሩ መሰረተ ልማቶች እንዳይወድሙ ባለው መሻት ሰላም እንዲከበርለት በተለያየ መንገድ ሲጠይቅ ቆይቷል።
ለጦርነት ተሰልፈው የነበሩ በርካቶች ግጭትና የፖለቲካ አለመግባባቶች ጠመንጃ በማንሳት እንደማይፈቱ ተገንዝበዋል፤ ፊታቸውንም ወደ ሰላም አዙረዋል፡፡ ጦርነት እንደማያዋጣ ተረድተው ውይይት ችግሮችን በዘላቂነት እንደሚፈታ በማመን ተመልሰዋል፡፡
በጠመንጃ የመሸናነፍና መብትን የማስከበር ሂደት ማብቂያ የሌለው አዙሪት ነው፤ ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥም ዋስትና የለውም፡፡
በዚህም የተነሳ “ብልህ ከሰው ይማራል” የሚለውን የሀገራችንን ብሂል መሠረት በማድረግ የሰላምን መንገድ መርጠው ለኢትዮጵያ ይበጃል ያሉትን ሊመክሩ ከተቀመጡት ትምህርት መውሰድ የብልህነት መገለጫው ነው።
ከዚህ በላይ ለምክክር የሚያነቃ የለምና በየአካባቢው ያሉና ሀሳብ አለኝ ያሉ ሁሉ በውይይት ሀሳባቸውን መስጠት እንደሚችሉ፣ ልዩነት መፍጠርና ለሀገር ይበጃታል የሚሉትን አካሄድ ማሳየት በመቻልና የሌሎችንም ሀሳብ በማድመጥ የጋራ መግባባት ላይ መድረስ እንደሚችሉ ማሳያ ነው፡፡
በቤተልሔም ግርማ