Fana: At a Speed of Life!

የሰው ሰራሽ አስተውሎት ጥረታችንን ፍሬ ማየት ጀምረናል – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 18፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የሰው ሰራሽ አስተውሎት ሀገራዊ ራዕይ እና ጥረታችንን ፍሬ ማየት ጀምረናል አሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ያሉት በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ለ6 ወራት የሰለጠኑ የመጀመሪያዎቹ የኤአይ ስታርትአፕ ሰልጣኞች ምረቃ ስነ-ስርዓት ላይ ነው።
የኢትዮጵያ መንግሥት ለዘርፉ የሰጠዉ ልዩ ትኩረት እና ለአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ባስቀመጠዉ ግልጽ አቅጣጫ ይህ ማዕከል ዕውን እንዲሆን አበርክቶው የጎላ ነው ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ዘርፉን ለማሳደግ ለሰጡት አመራርም ምስጋና አቅርበዋል።
ባለፉት ስድስት ወራት በኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ለኤአይ ስታርታፕ ማዕከል የቴክኒክ ስልጠና፣ የምርት ልማት ክህሎት እንዲሁም የገበያ ስትራቴጂ ስልጠናዎችን በስፋት እና በዓይነት በተደራጀ መልኩ መሰጠቱን ተናግረዋል።
ማዕከሉ ለስታርትአፖቹ ካቀረበው ስልጠና ባለፈ ምቹ የስራ ቦታ፣ ደረጃውን የጠበቀ የኤአይ ወርክሾፕ፣ የክላውድ ዳታ ሴንተር እና ከፍተኛ የኮምፒዩቲሽናል ሪሶርስ ተጠቃሚ አድርጓቸዋል ብለዋል።
በተጨማሪም ሜንተርሺፕ በመስጠት እና ዓለም አቀፍና ሀገር አቀፍ ኮንፈረንሶች ላይ እንዲሳተፉ በማድረግ በኢንስቲትዩቱ ከፍተኛ የኤአይ ተመራማሪዎች የቅርብ ድጋፍና ክትትል እንዲያደርጉ መደረጉን ገልጸዋል።
ድጋፉ ወጣቶቻችን ተሰጥዖዓቸውን ወደ ትልቅ እድል የሚቀይሩበት ምቹ መስክ ፈጥሮላቸዋል ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ እናንተ የኢትዮጵያ የቴክኖሎጂ አምባሳደሮች ናችሁ፣ ለኢትዮጵያ የላቀ የቴክኖሎጂ ጉዞ ልትተጉ ይገባል ብለዋል።
በለይኩን ዓለም
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.