የአካባቢ ሥነ ምኅዳር ደህንነትን እየጠበቀ ያለው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 19፣ 2018(ኤፍ ኤም ሲ) የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር የአካባቢ ሥነምኅዳር ደኅንነትን ለማረጋገጥ ጉልህ ሚና እየተጫወተ ነው አለ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት፡፡
የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ስትራቴጂክና ከፍተኛ አመራሮች በብሔራዊ ደኅንነት ዩኒቨርሲቲ ችግኝ በመትከል የተቋሙን ዓመታዊ የአረንጓዴ ዐሻራ ንቅናቄ በይፋ አስጀምረዋል፡፡
የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጄነራል አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን በዚህ ውቀት እንደገለጹት፥ ባለፉት ዓመታት እንደ ሀገር የተካሄደው የአረንጓዴ ዐሻራ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ተጨባጭ ውጤት እያስመዘገበ ይገኛል፡፡
መርሐ ግብሩ የሀገራችንን የተራቆተ መሬት በተለያዩ ተክሎች በማልበስ የደን ሽፋንን ማሳደግ መቻሉን አንስተዋል፡፡
የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር የአካባቢ ሥነምኅዳር ደኅንነትን ለማረጋገጥ ጉልህ አበርክቶ እንዳለውም ነው የገለጹት፡፡
እየተተከሉ ያሉ ችግኞችን ውጤት መመልከትና ማጣጣም እየቻልን ነው ማለታቸውን ከአገልግሎቱ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡